ኢትዮጵያዊው የግእዝ ቅኔ ሒደት ከየት እስከ የት
ከጌቴ ገሞራው
ከእምዋድላ ወዘዋሸራው
“…ዲቦራ ሆይ !! ንቂ ፡፡ ንቂ ፡፡ ቅኔውን ተቀኚ ፡፡…”
የአቤኒኤም ልጅ ባርቅ
መሳ = ፭÷፩ ::
“…ለወዳጄ ቅኔን እቀኛለሁ…”
ነቢይ ኢሳይያስ
ኢሳ = ፭÷፩ ::
“…በአዲስ ቅኔ ተቀኙለት…”
ባለበገናው ንጉሥ ዳዊት
መዝ = ፲፵፱ ÷ ፩ ::
“…ማንም ቅኔውን ሊተረጉመው አልተቻለውም…”
ወልደ ነጐድጓድ ቅዱስ ዮሐንስ
ራእ = ፲፬ ÷ ፪ ::
እሊኽ ብቻ አይደሉም ፡፡ በታላቅ መጽሐፍ ውስጥ የባለ “ቅኔነት “ ስማቸው ከብሮ ገንኖ የተጠራላቸው ሌሎችም ይኖራሉ ፡፡ ከእሊህም እንደ እነ ክሊያንትስና ኤፒመንድ መናንደርም የአሉት ዐበይት ባለ “ ቅኔያት ” ነበሩ ፡፡
ኾኖም በምድረ ግሪክና በምድረ እስራኤል የነበሩ እሊኽ ሊቃውንት የተናገሩ ትን “ ቅኔ “ ስንገልጠው ፣ “ ቅኔያቸው “ የምሥጢር መልዕክቱን የሚሰጠን በግዘፍ ብቻ ነው ፡፡ አያመራምረንም ፡፡ ምናልባትም ምሳሌያዊ ቢኾን ስንኳ “…ሰሙ እንዲህ ፡፡ ወርቁ እንዲያ …” ተብሎ የሚበለት የቅኔ ሥጋ የለውም ፡፡ በፍጹም ፡፡
ሌላው ቀርቶ “…ኳኛ ፤ ሙጫ ፣ ተሳሳቢ ፣ ድርድር ፣ የአገባብ ዝርዝር የዜማ መስበር ወዘተርፈ…” ለተሰኙና በኢትዮጵያዊው የቅኔ ቤት በሕግ የተከለከሉ ጸያፋትን ስንኳ ለመጠበቅ ኢትዮጵያዊው የግእዝ ቅኔ ዛሬም ጥንቁቅ ነው ፡፡
በአንጻሩ ግን የጥንታውያኑ ጥንታዊ “ ቅኔ ” ለዚህ ሩቅ አይደለም ፡፡ ለሕገ ፀያፍም ቢኾን እምብዛም አይጨነቅም ፡፡ በተጨማሪም ዝርው ነው ፡፡ ቤት የለውም ፡፡ ፈሳሲ ነው ፡፡ አይወሰንም ፡፡ ስለኾነም ከኢትዮጵያዊው የግእዝ ቅኔ በስፍሩ ፣ በቅርፁና በጠባዩ እጅና በጣም ይለያል ፡፡
ይኽንን ለመረዳትም እሊያ ጥንታዊያኑ ሊቃውንት “ ቅኔ “ በአሉት የእነርሱ ዘይቤ ውስጥ የቋጠሩት አመሥጥሮ እንደኢትዮጰያዊው የግእዝ ቅኔ ብዙ አያደክምም ፡፡ ዳግመኛም ይኸው “ቅኔያቸው” በግልጽ ደረቱ የታቀፈው ግልጽ የምሳሌ ትርጓሜና ቀጥተኛ የምስጋና ቃላት ብቻ ነው ፡፡ ማስረጃ ኸላይ የተጠቀሱትን ይመለከቷል ፡፡
ይኹን እንጂ ዛሬ በዚህ ጥናታዊ ጽሑፍ “ቅኔን ቅኔ የሚያሰኘው ምኑ ነው” ወይንም “…ባለቅኔ ማን ነው” ወደሚለው ክቡድ ጥያቄ በእጅጉ መጥለቅ አልፈልግም፡” ይልቅስ ኢትዮጵያዊው የግእዝ ቅኔ ሒደት ከየት እስከ የት የሚለውን ርእስ ብቻ በመተን ተን ግእዛዊውን የቅኔ ሠርጥ እከተላለሁ ፡፡
ለ. ለመኾኑ “ቅኔ” የሚለው ቃል ከየትኛው ግሥ ተገኘ ፡፡
“ የቅኔ አገባብ ” መጽሐፍ “ ቅኔ ” የሚለው ቃል ስለተገኘበት ግሥ ይነግ ረናል ፡፡ እርግጥ ነው ፡፡ እንደተለመደው ኹሉ አብዛኞቹ የኢትዮጵያዊው ግእዛዊ ቅኔ ቤተሰብኦች “ቀነየ = ገዛ ፡፡ ወይንም ተቀንየ = ተቀኘ ” ፡፡ ከሚለው ግሥ ቅኔ የሚለው ቃል ተገኘ ” ይሉናል ፡፡ ( በነገራችን ላይ ግሥ ማለት ገሥጋሽ ቃል ማለት ነው ፡፡ )
ኾኖም ግሥ የቀጸሉ ፣ በግሥ የበሰሉ ዋድላውያኑ ሊቃውንት ግን ከመጽ ሐፈ ኦሪት “…ኀበ አሳፍ ይቃኒ…” የሚለውን የግሥ ዕርባ ማስረጃ ያቀርባሉ ፡፡ በማስ ረጃቸው መሠረትም “ ቅኔ ” የሚለውን ቃል በ “ባረከ” ቤት ከሚገሠሠው “ቃነየ = ቃኘ” ከሚለው ግሥ የተገኘ ጥሬ ዘርእ ነው “ ይሉናል ፡፡
ስለቅኔ ዕውቀት ብሎ ገና በብላቴንነቱ…ከመኻል አዲስ አበባ ከፈረንሳይ ሠፈሩ…ከቀበና አቦ ደብሩ…ወጥቶ በዲማና በላስታ በዋድላና በዋሸራ በጎንጅና በልዩ ልዩ የቅኔ ቤተ ጉባኤያት የተንከራተተው የዚኽ ጽሑፍ አቅራቢም የሚያምነው “ቅኔ” የሚለውን ቃል በ “ባረከ” ቤት ከሚገሠሠው “ቃነየ = ቃኘ” ከሚለው ግሥ መገኘቱን ነው ፡፡
ሐ. የግእዛዊ ቅኔ ጥቅል መልክ ምን ዐይነት ነው ፡፡
ይኽ ኢትዮጵያዊው የግእዝ ቅኔ ኅንብርብሬ መልኩንና ብዙ ዐይነት ጠባዩን እንደጠበቀ ኾኖ “በሰምና ወርቅ” እንዲሁም “ጎዳና” በተሰኙ የቅኔ ዋና ዋና ክፍሎች የሚ መደብ ፣ የሕግ የተደነገገ የዜማ ልክ አለው ፡፡
ነገር ግን እንዲያው ስለአንድ ኹኔታ ስላወሳና የግጥም ቤት ስለመታ ብቻ ግጥም ያይደለ ነገር ግን በግጥም የሚገለጽ የምሥጢር ቋት ነው ፡፡ እዚህ ላይ ግጥም ኹሉ የቅኔ መገለጫው እንጂ ግጥም ኹሉ ቅኔ እንዳይደለ ልብ ይሏል ፡፡
ምክንያቱም ኢትዮጵያዊው የግእዝ ቅኔ ፈላሲ ወይም ዝርው አይደለም ፡፡ “ቤት” አለው ፡፡ ይሰማል ፡፡ “ ሕጋዊ ዜማ ” አለው ፡፡ በአሻው አይነጕድም ፡፡ “ልክ” አለው ፡፡ ጸያፍ የለውም ፡፡ “ ጨዋ ” ነው ፡፡
ይልቁንም በሰባት የቅኔ አገባብ መጻሕፍት ሕግጋቱ ተጠብቆ ከውሳጤ ልቡና ወደ አፍኣዊ ርቃቄ በድንገት ፈልቆ በድንገት የሚዘረፍ እንጂ በብዕር ተፀንሶ በወረቀት ላይ የሚወለድ አይደለምና ፡፡
እዚህ ላይ “ አማረኛ ቅኔሳ “ልንል እንችል ይኾናል ፡፡ አማረኛ ቅኔም ቢኾን በዝርው ንባብና በግጥም ከሚገለጹት የቅኔ ደቃልው (ዲቃሎች) ከኾኑት ኀብራተ ቃል በቀር የሚከተለው የወላጅ አባቱ የግእዙን ኢትዮጵያዊ ቅኔ ጠባይዕ ነው ፡፡
ይኽንን ለመረዳትም ምንም ስንኳ የቅኔ ቋንጣ ባይኖረውም “ጉባኤ ቃና ባልቴት ” በሚል የዚኽ ጽሑፍ አቅራቢ ከስምንት ዓመታት በላይ ቅኔ አስተምረው የመረቁትን የቅኔ ሊቅ የአማረኛ ቅኔ እንደምሳሌ ማየት ይቻላል ፡፡
እንደሚታወቀው “ጉባኤ ቃና” የግእዛዊው ቅኔ መጀመሪየ ክፍል ናት ፡፡ ባለ ኹለት ቤቷ ይኸቺ “ጉባኤ ቃና ” ታዲያ ለማንኛውም የቅኔ ጀማሪ ተማሪ ለኾን የቆሎ ተማሪ በጣም ታስቸግራለች ፡፡ እስኪለምዳት ፡፡ እኒኽ ሊቅም በተማሪዎቻቸው ላይ በእየ ዕለቱ የሚደርሰውን ይኸንኑ የተሜንና የ“ጉባኤ ቃና” ቅኔን ግኑኘነት አስመልክተው ነው እንግዲህ “ጉባኤ ቃና ባልቴት ” በሚል የሚከተለውን ቅኔ የዘረፉት F
“ጉባኤ ቃና ባልቴት የውሸቱ ዳንዴ ኧረ ምነው ይኾን እኔስ እውነት አትናገሪ ፣
አይቀርምና መቆም በገጸ መወድሰ ፈጣሪ ፣
አንድ እርሱ ነውና የኹሉ መረማሪ ፣
እኔም ዋነኛው ተቈርቋሪ ፣
የሚያስከፋብሽን ነገር ብመክርሽ አታንጐራጕሪ ፣
እማሆይሂ ጉባኤ ቃና በለመነሽ ጊዜ ተማሪ ፣
ተይ ግድ የለሽም ያለሽን ተዘከሪ ፣
ትይዋለሽና ለሠርክ አትንከርፈፍብኝ ዘዋሪ ፣
እያየሽ ትክ ብሎ ምሥጢር እንጀራን ስትጋግሪ ” ያሉት ፡፡
በኹለተኛ ምሳሌነት የምናቀርበውም ሌላውን የእኒኽኑ ሊቅ ቅኔ ነው ፡፡ ምክንያቱም እኒኽ ሊቅ እጅግ ሰፊ የቅኔ ቤተ ጉባኤ የአላቸውና በአሁኑ ጊዜ ወንበር ዘርግተው ጉባኤ አስፍተው በኢትዮጵያ የግእዛዊውን ቅኔ ዓለም ከሚመሩ ጥቂቶች አበው ሊቃውንት አንዱ ናቸው ፡፡
ዋናው ቁም ነገር ከላይ እንደተገለጸው ኹሉ የአባቱን የግእዛዊው ቅኔን አሠር የሚከተለው ይኸው አማረኛ ቅኔ ታዲያ የምሥጢር መልዕክቱን የሚገልጸው ዝርው ኾኖ ቤት በመታ ግጥምነቱ ብቻ አይደለም ፡፡ በሰምና ወርቅ ፍኖቱም እንዲህ እየተጓዘ ነው እንጂ ፡፡
“እንግዲህ እለፍ የቅኔ ተማሪ ምንም ሳትፈራ ጥቂት የልብ ድንቊርናን ክፉ ወንበዴ ፣
የምሥጢር ወታደር ያሬድ ባለመወድስ ጓንዴ ፣
አንገቱን ከልሎታልና በሚሥጢር ጐራዴ ፣
ድርሶና ደርሶ ሳያስበው
ካወቀበት ዘንድ ስለቱን በጉባኤ ቃና ምድረ ውጋዴ ፣
ተጠንቀቅሂ አያ ተማሪ እንዳታስትህ በዘዴ ፣
ብዙ ቄስ የሰፈረሰች መክፈልት ወረገዴ፡፡ ” በማለትም እኒኹ ሊቅ የቅኔ ተማሪያ ቸው በጊዜያዊ የመክፈልት ቁራሽ ደስታ ትምህርቱን እንዳይዘነጋ የመከሩበት የአማረኛ ቅኔ አለ ፡፡ ይኸም የሚያስረዳን ከኢትዮጵያዊው የግእዝ ቅኔ የተወለደው የአማረኛ ቅኔ ወላጅ አባቱ ኢትዮጵያዊውን የግእዝ ቅኔን የሚመስል መኾኑን ነው ፡፡
መ. ግእዛዊው የኢትዮጵያ ቅኔ መንገድ አለውን ፡፡
አዎ አለው ፡፡ እንደውም መንገዶቹ ልዩ ልዩ ስሞች አላቸው ፡፡ ከእሊኽም ጥቂቶቹን ስንኳ ለመጥቀስ ብንሞክር “ ገብረ ጉንዳን ፣ ዝምዝም ወርቅ፣ አታላይ ፣ ሸኾናይ ፣ ቆልቋይ ፣ ስብጥር ፣ አትሮንስ ፣ በዝብዝ ፣ ክብሶ ፣ ጉንጉን ፣ ራስ ማስር ፣ አበባ ለቀማ ፣ እንጉዳይ ፣ ሥርዋፅ ፣ ራስ አንሣ ፣ አራት ራስ ፤ ተርሙስ ፣ ፍርን ዱስ ” የሚባሉት ለምሳሌ ያህል ብቻ ከሚጠቀሱት እጅግ በጣም ጥቂቶቹ ናቸው ፡፡
ከእነዚህ ውስጥ “ፍርንዱስ” የተባለው የቅኔ መንገድ በተለይ “የቅኔ ጉልበት” የሌላቸው…አልፎ አልፎም ጠንካሮ የቅኔ መምህራን ሳይቀሩ የግእዝ ቋንቋ የማይሰማውን ዕድምተኛ ለመያዝ ሲሉ የሚያዘወትሩት ቀላል መንገድ ነው ፡፡
“ ፍርዱንስ ” ማለት የግእዝና አማረኛ ቃላት ስለተቀላቀለበት ክፍትፍት ያለ፣ አማረኛው የግእዙን ተነሽ ተጣይ ፣ ሰያፍና ወዳቂነት ተመስሎ የሚነገርበት ጠባይ ያለው የቅኔ መንገድ ነው ፡፡
ይኽንን የቅኔ መንገድ ጸሐፌ ተውኔት ፣ ደራሲና ተዋቂ የቅኔ መምህር በነበሩት በሊቁ ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ የቅኔ ዘረፋ ላይ እናገኘዋለን ፡፡ ወቅቱ በኢጣሊያ ስለተወረረችው ሀገራችን ኢትዮጵያ ጉዳይ ንጉሡ ቀዳማዊ ዓፄ ኃይለ ሥላሴ “ ጄኔቭ ” በተሰበሰበው ሊግ ኦፍ ኔሽን ላይ ስለኢትዮጵያ አቤቱታ እያቀረቡ ነበር ፡፡
ኢትዮጵያን ለወረረው የኢጣሊያ መንግሥት የወገነው ያ የፈረንጆቹ ጉባኤ ግን “ እሺ ፡፡ ” ግን ነገ… ቆይ ፡፡ ተነገ ወዲያ ፡፡ ” እያለ በንጉሠ ነገሠት ቀዳማዊ ዓፄ ኃይለ ሥላሴ የቀረበለትን የኢትዮጵያን የአቤቱታ ድምፅ ሰምቶ ለመፈፀም አመነታ ፡፡
በዚህ ጊዜ ነው ፡፡ ሊቁ ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ በኢትዮጵያ ላይ የተፈጸ መውን የፈረንጆቹን ግፍዕ በቅኔ መውድሳቸው ለዓለም (ግማሹ) ላይ በፍርንዱስ የቅኔ መንገድ “ በዴኔቭሂ…” ሲሉ ቅኔ የዘረፉት ፡፡ ቅኔያቸውም F
“በዴኔቭሂ አመ ተፀንሰ ዘኢትዮጵያ አለኝታ ፣
የቱሞሮ እናት እሺ ነገ ለብሂለ ኦራይት ወለደታ ፣
ወእሺ ነገ እኅትነ እምድኀረ ወለደት መንታ ፣
ሕማማ ከመትዝክር ለአፍተር ቱሞሮ ተቀበለታ ፡፡ ” የሚል ነው ፡፡
ሰ. የቅኔ ግእዛዊ ዐይነቶች ስንት ናቸው ፡፡
የቅኔ ዐይነቶች “የጎንጅ ፣ የዋድላ ፣ የዋሽራ” ተብለው ይለያሉ ፡፡ ልዩነታቸ ውም በግሥ አገሣሥ ዕርባ ፡ በሚገቡና በማይገቡ የቃላት ጠባይዕ ፡ በዜማ ልክ ፣ በቅኔ አገባብ ሕግ ፡ በቅኔ ስደራና በልውጥ ያሬዳውያን የዜማ ስፍሮች ወዘተርፈ ነው ፡፡
እነዚህ “ጎንጅና ዋሸራ” የተባሉት መካናተ ቅኔ (ሥፍራዎች) በጎጃም ፣ “ዋድላ” የተባለው መካነ ቅኔም በወሎ ክፍለ ሀገር (ክልል) ይገኛሉ ፡፡ እነዚህ አውራጃዎች ለብዙ ዓመታት የቅኔ ትምህርት የአብነት ቦታ ኾነው በመቆየታቸው ቅኔዎቹ በእነርሱ ስም ሊጠሩ በቅተዋል ፡፡
ረ. የቅኔ ግእዛዊ ዋና ዋና ክፍሎች ስንት ናቸው ፡፡ ስንት ስንት ቤትስ አላቸው ፡፡
፩ኛ. ጉባኤ ቃና—ቅኔ—ኹለት ቤት ነው ፡፡
፪ኛ. ዘአምላኪየ—ቅኔ—ሦስት ቤት ነው ፡፡
፫ኛ. ሚ በዝኁ—ቅኔ—ሦስት ቤት ነው ፡፡
፬ኛ. ዋይ ዜማ—ቅኔ—ሦስትም ስድስትም ቤት አለ ፡፡
፭ኛ. ሥላሴ—ቅኔ—ሦስትም ስድስትም ቤት አለ ፡፡
፮ኛ. ዘይእዜ—ቅኔ—ሦስትም ሰባትም ቤት አለ ፡፡
፯ኛ. መወድስ—ቅኔ—ኹለትም ሰባትም ስምንትም ቤት አለ ፡፡
ሠ. ግእዛዊው ኢትዮጵያዊውን የግእዝ ቅኔን መጀመሪያ የደረሰው ማን ነው ፡፡ እንዴትስ ደረሰው ፡፡
አንድ አንዶች ተዋነይን የቅኔ ጀማሪ ወይም የቅኔ አባት አድርገው የሚያቀርቡ አሉ ፡፡ ነገር ግን ሊቃውንት የተጻፉ መጻሕፍት ፣ ባልቴቶችም የታሪክ ቀለማት ናቸውና ተዋነይንን በቅኔ አባትነት አይነግሩንም ፡፡ በፍጹም ፡፡ ምክንያቱም ተዋነይ የቅኔ ልጅ እንጂ የቅኔ አባት አይደለምና ፡፡
የቅኔ አባት ፣ የቅኔ ደራሲማ ዋድላዊው ዮሐንስ ገብላዊ ነው ፡፡ ይኽንኑም የቅኔ አገባብ መጽሐፋችን ሲነግረን “አደራሱስ እንደ ምን ነው ቢሉ” ሲል ይጀምራል ፡፡ በማያያዝም “…ቅኔን ቅዱስ ያሬድ ጀምሮት ቢያይ ዮሐንስ ገብላዊ እንዲገለጽለት አውቆ ሱባኤ ገባ ፡፡ ተገልጾለትም ከቅዱስ ያሬድ አያይዞ ወስኖታል ፡፡ ደርሶታል…” ይለናል ፡፡
ከዚህ በኋላ ባለቅኔው ዮሐንስ ገብላዊ ለባለቅኔው ወልደ ገብርኤል ባለቅኔው ወልደ ገብርኤል ለባለቅኔው መምህረ ሠምረ ክርስቶስ (ሠምረ አብም ይለዋል) አስተም ረዋል ፡፡ ባለቅኔው መምህር ሠምረ አብ ያስተምሩ በነበረበት ዘመን ንጉሡ ዓፄ በእደ ማርያም ነበሩ ፡፡
በዚህ ኢትዮጵያዊው የግእዝ ቅኔ ምክንያት በንጉሡና በመምህሩ መሐል ክርክር ተፈጠረ ፡፡ ጭቅጭቅ ተነሣ ፡፡ ተያይዘው ሱባኤ ገቡ ፡፡ ያን ጊዜም የቅኔ መጀመሪያ ክፍል የኾነው የጉባኤ ቃና ቅኔ ምሥጢር ከመምህሩ ይልቅ ለንጉሥ ዓፄ በእደ ማርያም ተገለጸላቸው ፡፡
የቅኔ አገባብ መጽሐፍም ይኽንኑ ሲያስረዳ “…መንፈስቅዱስ የንጉ ሡን ልብ መታው ፡፡ ቀኑም ቃና ዘገሊላ ነበር ፡፡ በዚያን ጊዜም “ቅኔ የምትለው ነገር ዝም ብሎ ልፍለፋ ነው” እያሉ ከመምህር ሠምረ አብ ጋራ ሲጣሉ የነበሩትና “እውነት ከእግዚአብሔር ከኾነማ ” ብለው ከመምህር ሠምረ አብ ጋራ ሱባዔ የገቡት ንጉሥ በእደ ማርያም በመንፈስ እንደ ተመሉ አፈፍ ብሎ ተነሥተው F
“ድኅረ ተሰብረ አጽንዖ ለሰብእናነ ልኍኵት ፣
ለብሓዊ ክርስቶስ በማየ ሐዲስ ጥምቀት ” በማለት ቅኔ ዘረፈ ፡፡
“የዚህ ቅኔ ትርጓሜም ሸክላው ሕይወታችን ከተሰበረ በኋላ ጥበበኛው ክር ስቶስ በአዲስ የጥምቀት ውኃ መልሶ አጸናው” በማለት የክርስቶስን አዳኝነት የሚገልጽ ውብ ቅኔ ነበር ፡፡
ከዚህ በኋላ ንጉሡና ዮሐንስ ገብላዊ በዚያው በአታቸው ውስጥ ኾነው ከጉባኤ ቃና እስከ መወድስ የአሉትን ከላይ የተጠቀሱትን ሰባቱ ቅኔያት እየተራ ተቀኝተዋል ፡፡ እነዚኽ ቅኔያትም ያላቸውን የአሰያየም ፤ የሐረግ ፣ የቤትና የአነጋገር ትርጓሜያት ምሳሌ እንዳንዘረዝር ሐተታው ብዙ ነው ፡፡
ሸ . ተዋነይ የማን ተማሪ ነበር ፡፡
ባለቅኔው ተዋነይ የመምህር ኤልያብ ተማሪ ነበር ፡፡ የቅኔውን የትም ህርት ተዋረድ ሐረግ ተከትለን ወደታች ስንወርድ ከንጉሡ ዓፄ በእደ ማርያም ጋራ በቅኔ ምክን ያት የተጣሉት መምህር ሠምረ አብ ፣ ለመምህር ልሂብ ፣ መምህር ልሂብ ፣ ለመምህር ኤልያብ መምህር ኤልያብ ለድድቅ ወልደ ማርያምና ለተዋነይ አስተምረዋል…ቅኔውን ፡፡
(በነገራችን ላይ ባለቅኔ ስንል ወዲያው በአየው ነገር ድንገት ቅኔ የሚዘርፍ እንጂ ግጥም በወረቀት ጽፎ የሚያነብብ ማለት እንደአይደል ልብ ይሏል ፡፡)
የመምህር ተዋነይ የቅኔ ዘመን ከባድ ነበር ፡፡ ምክንያቱም ብዙም ሳይቆይ ቅኔንና ዜማን…ትርጓሜንና ጥበብን…ጥበብንና ቅርስን…ባህልንና ታሪክን የዋደመው ግራኝ ነገሠ ፡፡ መንግሥት ተፋለሰ ፡፡ በዚኽን ጊዜ ባለቅኔው መምህር ተዋነይ ደቀ እሲጢፋ ፡፡ ባለቅኔው ድድቅ ወልደ ማርያም ዳውንት ገቡ በስደት ፡፡
ኋላ ተዋነይ ከደቀ እስጢፋ ሲወጣ የቀለም አባቱ መምህር ኤልያብ ሞቱ ፡፡ እርሱም እንጂ ኩሩ ነበርና “ከወንድሜ ከድድቅ ወልደማርያምስ አልጠይቅም” ብሎ ተወው” የጎንጅ አገባብ ማነሱ ዕርባ ቅምር አለመኖሩ ስለዚህ ነው ፡፡ ምክንያቱም የጎንጅ ቅኔ መንገዱ ተወነያዊ ነውና ፡፡
ኾኖም መምህር ተዋነይ እንዲህ ገናና ባለቅኔ ኾኖ ሳለ አንድ አንዶች ደናቊርት “ተዋነይ የስሙን ገናንነት ያህል ብዙ ቅኔ አናነብለትም…” ሲሉ ይደመጣሉ ፡፡ የሊቁ ተዋነይ የቅኔ ቋንጣ እስከ ዛሬ ድረስ በእኛ ዘንድ ይገኛሉና ፡፡
ቀ. ከእነተዋነይ በኋላ ቅኔ እንዴት ቀጠለ ፡፡
ቅኔ በስፋት የቀጠለው በድድቅ ወልደ ማርያም ነው ፡፡ እሳቸው ከሰው አል ተለዩም ነበርና አገባብና ዕርባ ቅምር ይዘው ተገኝተዋል ፡፡ ዳውንት የጨረቃ በሚባል ሀገርም ሰባት መምህራን “…ድድቅ…ድድቅ…” እየተባሉ ሲያስተምሩ ኑረዋል ፡፡ በነገራችን ለይ አገባብ ዕርባ ቅምር ማለት የቅኔ ሒደት ሕግጋት ናቸው ፡፡
ከዚህ በኋላም ሰባት አዋጅ ሰባት ዕርባ ቅምር ፣ ሰባት አገባብ የተጻፈለትን የቅኔ ሙያ ሰባተኛው ድድቅ ለስላና ወልደማርያም ፣ ስላና ለማዕበል ወልደ ሕይወት ፣ ማዕበል ወልደ ሕይወት ለአለቃ ገብረ ኢየሱስ ፣ አለቃ ገብረ ኢየሱስ ለአለቃ ቡሩኬ ፣ አለቃ ቡሩኬ ለአለቃ መርዓዊ አስተምረዋል ፡፡
በ. የቆሎ ተማሪ ማለትስ ምን ማለት ነው ፡፡
ይኽ ጥያቄ እዚኽ ላይ መነሣቱ በእጅጉ ተገቢና ደግ ነገር ነው ፡፡ ስለኾነም የቆሎ ተማሪ ማለት ለዕውቀት ሲል ከወገኑ ተለይቶ ፣ ቀዬውን ጥሎ ፣ ከሀገሩ ኮብልሎ ከውሻ ጋር ታግሎ ፣ ቢያገኝ ቊራሽ እንጀራ ቢያጣም ጥሬ ለምኖ ፣ ደበሎ ለብሶ ፣ አኩ ፋዳ ተሸክሞ ፡ ጕዝጓዝ ተንተርሶ የሚኖር ፣ ለቀለም የሚሰደድ ፣ ለጥበብ የሚንከራተት የዕውቀት ሊቅ ፣ የጥበብ ምንጭ ፣ የአለፈውን የሚረዳ የመጻኢውን ኩነት አርቆ ተመል ካች ማለት ነው ፡፡
ተ. የቅኔ ትምህርት እንዴት ይሰጣል ፡፡
አንድ ተማሪ ወደማንኛውም የቅኔ ቤት ሲሔድ በአብዛኛው ከቤተ ሰብኡ ተሠውሮ ነው ፡፡ የሚይዘው አንዲት አኩፋዳ አንዲት ለምድና ነጠላ አይሏት ጋቢ መለስ ተኛ ኩታ ሊኾን ይችላል ፡፡ ስንቁ ግን የማርያም ስምና የገበሬው ችሮታ ነው ፡፡
ተማሪው ከሔደበት ተማሪ ቤት ሲደርስ ከየት መጣህ አይባልም ፡፡ ከእርሱ የቀደሙ የቤተ ጉባኤው ተማሪዎች “ ኖር ” ብለው አክብረው ፣ መቀመጫ ለቅቀው እግ ሩን አጥበው ፡ ከለመኑት አኩፋዳ ቁራሽ አዋጥተው ምኝታ ሰጥተው በእንግድነት ተቀብ ለው ያሳድሩታል ፡፡ በማግሥቱ መምህራቸው ፊት በተማሪዎች አለቃ አማካይነት ይቀር ባል ፡፡
መምህሩ ስሙንና የመጣበትን ምክንያት ጠይቀውና አረጋግጠው ጎጆና ባል ደረቦች እንዲሰጡት የተማሪዎቻቸውን አለቃ ያዙለታል ፡፡ ከአንዱ የተማሪ ጎጆ ተጠግቶ ተዳብሎ እንዲኖር አስቀጻይ ባልደረባ ይመደብለታል ፡፡ የልመና መንደርም እንደሌሎቹ ወይም ከሌሎ ጋራ ተካፍሎ ይከለልለታል ፡፡ ትምህርቱን ይቀጥላል ፡፡
በቅኔ ቤት የኾነ እንደኾን መጀመሪያ ግሥ እያጠና ከእርሱ በዕውቀት በዕድሜ ከፍ ለአሉት እየለመነ እንጨት ሰብሮ እግር አጥቦ ትምህርቱን መቀጸሉን ይቀጥ ላል ፡፡ ግሥና ነባር ቃላት ከማጥናት ጋራ በእየዕለቱ የሚዘረፈው የየኔታንና ከየኔታ በታች የአሉት የቅኔ ዘራፊዎችን ቅኔ አሠር በመከተልና የራሱን ቅኔ በማነፃፀር ምሥጢር ለማደላደል ይሞክራል ፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ ትምህርቱን በመቀጸል ከጉባኤ ቃና እስከ መወድስ የቅኔ መሙላት ደረጃ ይደርሳል ፡፡
ቸ. ቅጸላ ማለት ምንድን ማለት ነው ፡፡
የማያቋርጥ ጥናት እንደማለት ነው ፡፡ ግሥ የሚቀጸለው በቃል ነው ፡፡ ዜማ ልኩ የአእመረ…ወዘተርፈ እንዲሁ ፡፡ እንደገናም በእየዕለቱ የተዘረፈውን ሙሉ ቅኔ መጀመሪያ ዘርኡን በቃል ይያዛል ፡፡
በማስከተልም የቅኔውን ጥሬ ፍቺ…እንደገና ርቃቄውን…እንደገናም የቅኔያቱን ሙያ አሰጣጥ…በቃል ወስኖ ለመያዝ ደጋግሞ መላልሶ በትኩረት ማጥናት ማለት ነው ቅጸላ ማለት ፡፡
ነ. የቅኔ ትምህርት ደረጃ አለውን ፡፡
እወ ፡፡ አዎን አለው ፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ… አንድ ተማሪ ከላይ የተጠቀሱትን ከጉባኤ ቃና እስከ መወድስ ያሉት ሰባት ቅኔያት በእየተራ እየተሰጡትና የሐረጋቸውን ስፋት ጥበት የዜማ ልካቸውን መስፈርት በእየቀኑ ቅኔ እየቈጠረ ለየኔታና ከየኔታ በታች ለአሉ የቅኔ ዘራፊዎች በሚያደርገው የቅኔ ነገራው እየተለማመደና እያወቀ በጥሩ ኹኔታ ምሥጢርን ሲያደላድል “ ቅኔ ሞልቷል ” ይባላል ፡፡
ኹለተኛው ደረጃ ….. በዚሁ የሙሉ ቤት ቅኔ ውስጥ የነበረው ተማሪ እየበሰለ ሔዶ ወደ አገባብ ቅጸላ ሲሸጋገር ቅኔን የማስነገር ኃላፊነት ይሰጠዋል ፡፡ “ቅኔን አስነጋሪ “ ይባላል ፡፡ ጀማሪያንም ኾኑ ቅኔ የሞሉ ተማሪዎች ፊቱ ቆመው የቈጠሩትን ቅኔ ሲነ ግሩት እርሱም በተራው መምህሩን ተክቶ ያርምላቸዋል ፡፡
በሦስተኛ ደረጃ የቅኔ አገባቡንም የግሥ ቅጸላውን የመጀመሪያ ክፍል ሲያጠናቅቅ ቅኔን እያሰበ ወይም ቈጥሮ ከመንገር ይልቅ ወዲያው ወዲያው ማፍሰስ ስለሚጀምር ወደ ቅኔ ዘረፋ የቅኔ ሊቅነት ማዕረግ (ረዳት ፕሮፌሰርነት) ይሸጋገራል ማለት ነው ፡፡ “ ዘራፊ ” የሚለውን የቅኔ ማዕረግም ያገኛል ፡፡ ከላይ የተጠቀሱትንና ሌሎችንም የቅኔ ጓዞችን ጠንቅቆ ቀጽሎ ሲጨርስም በቅኔ መምህርነት ተመርቆ ይወጣል ፡፡
አ. የቅኔ መቀኘትና የቅኔ መዝረፍስ ልዩነቱ ምንድነው ፡፡
አስቦ ፣ ጊዜ ወስዶ ቃል ከቃል ፣ ግሥ ከግሥ አገናኝቶ ቅኔ የሚያደርግ ቅኔ ቈጣሪ ነውና “ ቅኔ ተቀኘ” ይሰኛል ፡፡ በሚያየው በሚሰማው ሌላውን ቀድሞ ዐውቆ ቅኔን የሚነጥቅ ግን “ ዘራፊ ” ይሰኛል ፡፡
በብዙዎች የሚታወቀውንና የተለመደውን የእማሆይ ገላነሽ የቅኔ ዘረፋን እንደምሳሌ እዚህ ላይ ይጠቅሷል፡፡ በብላቴንነታቸው ነው፡፡ የኋላ ኋላ የጎንጂ ስመጥር የቅኔ ንግሥት ልትሆን የዚያን ጊዜዋ ሕፃኒቱ ገላነሽ በሴቶች መቋሚያ ነበረች፡፡
ዕለቱም በአለ ደብረ ታቦር ሊኾን ይችላል ፡፡ በወቅቱ ደግሞ የቅኔ መምህሩ ወላጅ አባቷ በቅኔ ማኀሌቱ ውስጥ በካህናቱ መኻል ቆመው “መወድስ ቅኔ” እየዘረፉ ነበር ማለት ነው ፡፡ ከሚዘርፉት የመወድስ ቅኔያቸው መክፈያ (አጋማሽ) ሲደርሱ “በታቦርሂ አመ ቀነፀ መለኮትከ ፈረስ ፣ ” አሉ ፡፡
ነገር ግን አልጨረሱትም ፡፡ በብላቴናይቱ ሴት ልጃቸው ተነጠቁ ፡፡ ገና የቅኔ ፊደል ትምህርት ስንኳ ያልጀመረችው ብላቴናይቱ ልጃቸው ገላነሽ በዚያ የሴቶች መቋሚያ ኾና “ ኢክህሉ ስሂቦቶ ሙሴ ወኤልያስ ፡፡ ” በማለት በሕሊናቸው ውስጥ የነበረውን ቀጣዩን የቅኔ ሐረግ ነጠቀቻቸው ፡፡
እሳቸውስ መች የዋዛ ናቸውና ሴት ልጅ በዐደባባይ ትናገር ዘንድ አይገባም ፡፡ የሚለውን የቅዱስ ጳውሎስን ቃል በመጥቀስ ለዚያች የቅኔ ሊቅት ብላቴና ልጃቸው “ ከመ አነ ሰማዕኩኪ አይስማዕኪ ጳውሎስ” (እኔ እንደ ሰማኹሽ ቅዱስ ጳውሎስ አይስማሽ) በማለት መልሰውላታል ፡፡ የእሳቸው የቅኔ ትርጉም “መለኮት ፈረስህ በታቦር በዘለለ ጊዜ” የሚል ሲኾን ብላቴናይቱ ገላነሽም “ሙሴና ኤልያስ ይስቡት ዘንድ አልቻሉም” በማለት ነበር ቅኔውን የነጠቀቻቸው ፡፡
አዎን የቅኔው ሊቅ አባቷ አልተሳሳቱም ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ስለሴቶች በአደባባይ ይናገሩ ዘንድ አስመልክቶ የጻፈውን በመጥቀስ ነበር የዚያን ግዜይቱ ብላቴና ልጃቸው ገላነሽን “ እኔ እንደ ሰማሁሽማ ጳውሎስ አይሰማሽ ” ያሉት ፡፡
ያም ኾነ ይኽ የእኒያን የታወቁ የቅኔው ሊቅ አባቷን ቅኔ በድንገት የዘረፈችው (የቀማችው) ብላቴናይቱ ገላነሽ ምን ብትቀምስ ይኾን የሚለው ይቆየንና ቅኔ መዝረፍ ማለት ሌላው ያሰበውን ፣ አስቦ የጀመረውን ቅኔ ሐረግ በድንገት መንጠቅ ማለት መኾኑን ይኽ የቅኔ ንግሥቷ የእማሆይ ገላነሽ ታሪክ ያስረዳናል ፡፡
ከ. ከዚህ ሌላ የቅኔ ስሞች አሉን ፡፡
አሉ ፡፡ እሊኽ ስሞችም ልክ በሀገራችን ለጀግኖቻችን በቀደመው ዘመን “በዝብዝ ፡፡ ታጠቅ ፡፡ ኮስትር ፡፡ ጠቅል ፡፡” በሕዝብ የሚሰጡ ሕዝብ ለሀገራችን ጀግኖች የሚያወጣቸው የጀግንነት የዕውቅና የፈረስ ስሞች እንደ ነበሩ ይታወቃል ፡፡
ልከ እንደዚኹ ኹሉ በቅኔውም ዓለም “ድድቅ ፣ ማዕበል ፋንቴ ፣ ጌቴ ገሞራው ፣ አባ ስበር ፣ እሳቱ ፣ ግጨው ፤ መብረቁ ፤ ነበልባሉ ፣ ነጐድጓድ ናደው ፡፡” እየተባለ የሚጠራ የቅኔ ስም ያላቸው ከቅኔያቸው ነዲድነት የተነሣም የምሥጢራት ፍም የሚተፉ የቅኔ ሊቃውንት ነበሩን ፡፡ ዛሬም አሉን ፡፡
ኸ. ግእዛዊው ቅኔ አሁን ያለበት ደረጃ ምን ላይ ይገኛል ፡፡
እንደሚታወቀው ኢትዮጵያዊው የግእዝ ቅኔ አብዛኛው በቃል የሚሰጥ በመኾኑ ከአንዱ ወደ አንዱ ትውልድ በተሟላ ኹኔታ መተላለፍ አልቻ ለም ፡፡ (የደሴውን የየንታ መጽሔትን ዐረቤ መጽሐፈ ግሥ እንደ ምሳሌ ይጠቅሷል) ያሉትም የዚህ ኢትዮጵያዊው የግእዝ ቅኔ ቤተ ጉባኤያት የተዳከሙ ናቸው ፡፡
በገጠር ያሉት የቅኔ ሊቃውንትም “ አይዞህ ” ባይ ደጋፊ በማጣት በእርጅና በበሽታ ቤት ሲውሉ ፣ በሞት ሲያልፉ የሚተካቸው እየጠፋ ነው ፡፡ ለምኖ በልቶ በመኖር የመማር የተማሪው ተስፋም በኑሮ ክብደት እየጨለመ ነው ፡፡
ይኽም ባይኾን የልመና ሥርዓቱ መወገድ አለበት ፡፡ በአጠቃላይ አሁን ባለው ዘመናዊ ሁኔታ ከባድን የኑሮ ችግር ተቋቁሞ ይኽንን ኢትዮጵያዊው የግእዝ ቅኔ ትምህርት እስከ መጨረሻው የሚማር ተማሪ ቊጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ነው ፡፡
ወ. ይኽ ኢትዮጵያዊ የግእዝ ቅኔ በነበረበት ተስፋፍቶ እንዲቀጥልስ ምን መደረግ አለበት ፡፡
ትልቁ ቁም ነገር የአለው እዚኽ ጥያቄ ላይ ነው ፡፡ ከላይ እንደአየነው ይኽ የቅኔ ሙያ ዘመን በመጣው ቋንቋ “ የዚኽ ወይም የዚየኛው ብሔር ” ተብሎ በማይመደበው የመላው ኢትዮጵያውያን ጥንታዊ ቋንቋ በኾነው ልሳነ ግእዝ የሚገለጽ ነው ፡፡
ግእዝ ደግሞ ከሰማንያ አንድ በላይ ለሚገመቱት የኢትዮጵያውያን ክቡራን ቋንቋዎች ኹሉ መሠረት ነው ፡፡ የቅኔው ሙያም በሌሎች ዓለማት የሌለ በሀገራችን ብቻ የሚገኝ የሀገራችን የጥበብ ቅርስ ነው ፡፡
- ቅኔ የታሪካችን አካል ነው ፡፡
- ቅኔ የኢትዮጵያዊነት አንድ አሻራ ነው ፡፡
- ቅኔ ኪነ ጥበብ ነው ፡፡
- ቅኔ በቃልና በሕሊና የሚያዝ እንጂ በወረቀት የማይሰፍር በውሳጤ አእምሮ ካለ ክሂል ድንገት ፈልቆ ድንገት የሚገነፍል ልዩ ጸጋ ነው ፡፡
ስለኾነም F
በውኑ ታዲያ የኢትዮጵያ ሀገራችንን ስም በሌሎች ዓለማት በኪነ ጥበባዊ ክብር ሊያስጠራ የሚችል ይኽንን ኢትዮጵያዊ ታላቅ ሙያ እንደ ዘመናዊው የሥነ ጥበብና የሥነ ጽሑፍ ትምህርት ጥቅም ላይ ማዋል አይቻልምን ፡፡ ይቻላል ፡፡ አዎ አንድ ነገር ማድረግ ይቻላል…አንድ ነገር ብቻ………….
ይኸውም በገጠርም በከተማም የሚገኘው ትውልድ ጥቅሙን ተረድቶ የቅኔን ሙያ ያውቅ ያጣጥም ዘንድ ይገባል ፡፡ ለዚሁም በዘመናዊ ኹኔታ በትምህርት መረጃ መሣሪያዎች በመታገዝ በክፍል ውስጥ ያለ ረኃብና ጥም ፣ ያለመንገላታትና ብዙ ዓመታትን ሳይወስድ በአጭር ጊዜ መማርና ማስተማር የሚቻልበት ኹኔታ መፈጠር አለበት ፡፡ ቢያንስ ኢትዮጵያዊውን የግእዝ ቋንቋ ማስፋፋት…………
ለመኾኑስ የግእዝ ቋንቋና የግእዝ ቅኔ ከመላው ዓለም ይልቅ በብቸኝነት በሚነገርባትና ግእዛዊው ቅኔ በሚፈስስባት የቅኔና የግእዝ ሀገር ኢትዮጵያ ውስጥ እስከ አሁን ድረስ ዘመናዊ የቅኔ ትምህርት ቤቶች አለመኖራቸውስ አይገርምምን ፡፡
ለዚህስ የታሪክ ተጠያቂው ማን ይኾሆን…ይኽንን ኢትዮጵያዊ የቅኔ ሙያ ከነግእዝ ልሳኑ በሀገርና በዓለም ደረጃ የምናስተዋውቅበትና የምናስፋፋበት ጊዜና ዘመን አሁን ነው ፡፡
አዎ ይኽንን ሀገራዊ የቅኔ ሙያ በተለይ ይኽ ትውልድ እንዲያውቀውና በተተኪው የነገው ትውልድ ውስጥም አብቦ እንዲያፈራ ማድረግ አለብን ፡፡
ስለዚህም ቀዳማይ ፣ ከልዓይ ፣ ሣልሳይ ፣ ራብይና ኀምሳይ ማለትም አንደኛ ፣ ኹለተኛ ፣ ሦስተኛ ፣ አራተኛ እየተባለ የክፍል ማዕረግና ደረጃ የሚሰጥበት በትምህርት መስጫ መሳሪያዎች የተደገፈ የግእዝ ቋንቋና የቅኔ ትምህርት ቤት መክፈት አለብን ፡፡
የቅኔ ትምህርት አሰጣጡም በሥርአተ ትምህርት የሚካተትበትን ሁኔታ አመቻችተን ትውልዱ ተጠቃሚ እንዲኾን ማድረግ አሁን የኛ የታሪክ ኃላፊነት ተራ ይኾናል ፡፡ አዎ ፡፡ ዛሬ ፡፡ አሁን ፡፡
ተፈጸመ
ወርኃ መስከረም ፩ ቀን ፪፼፲፪ ዓ. ም
ከጌቴ ገሞራው
ከእምዋድላ ወዘዋሸራው