የበዓለ መስቀሉ የዜማ ጣዕም

በምልጣንና በእስመ ለዓለም

ከጌቴ ገሞራው

ዘእምዋድላ ወዘዋሸራ

           ከዘጠኙ ንዑሳን በዓላት አንዱ የኾነው በዓለ መስቀል ‹‹…ወወሀብኮሙ ትዕምርተ ለእለ ይፈርሑከ—-ለሚፈሩሕ ምልክትን ሰጠኻቸው ›› የሚለውን የትንቢት መምሪያ የብሉይ ኪዳኑን በዓልም የተስፋ መሠረት ፤ የንግሥት ዕሌኒንም ታሪክ የተስፋ ፍጻሜ መገ ለጫ አድ ርጓል ፡፡ ስመ በዓሉም በቤተ ክርስቲያን ስያሜ “ዘመነ መስቀል ፡፡ ሰሙነ መስቀል” ይባላል ፡፡ አበውን ከውሉድ ፤ ብሉይ ኪዳንን ከሐዲስ ኪዳን ተስፋን ከእውነት ፤ መሠረትን ከፍጻሜ ያዳ መረ ያጣመረ ነውና “ደመራ” ተሰኝቷል ፡፡

          ዋሸራዊው መጽሐፈ ግሥ “ደመረ = አንድ አደረገ” ይልና “ደመራ” የሚለውን ጥሬ ቃል ያወጣል ፡፡ “ ደመራ ” ማለትም አንድ ማድረግ (አንድ መኾን) ማለት ሲኾን ቃሉ ለእኛ ኢትዮጵያውያን ልዩና ጥልቅ ምሥጢር አለው ፡፡

          ይኸውም ፍቅር ስቦት እኛን ለማዳን የመጣ ክርስቶስን ፍጹም አዳኝነቱን የምንረ ዳበት ነገረ መስቀሉ ሕያው ነውና ፡፡ አንድም አይሁድና አይሁድን የመሰሉ የዘመናችን መናፍ ቃን ቢክዱትም ለምናምንበት ለእኛ ግን “መስቀል ኃይልነ” = ኃይላችን ፡፡ “ጽንዕነ” = መጽና ኛችን ፡፡ “ቤዛነ”=ድኅነትን የምናገኝበት መመኪያችን ነውና ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹…አንሰ ሐሰ ሊተ ኢይዜኀር ዘእንበለ በመስቀሉ ለእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ–ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ የምምካበት የለኝም…›› የሚለውን ሐዋርያዊ መመሪያውን ሰጥቶ ናልና ገላ = 6÷14 ፡፡

           ሐዋርያው ስለነገረ መስቀሉ የሚያስተላልፍልን ግልጽ የመልዕክተ ክታቡ መመሪያ በዚኽ ብቻ የተወሰነ አይደለም ፡፡ እንደውም በእየጎዳናው እየጠበቁ በስሁት አነጋገራቸው ከምን መካበት የክርስቶስ ቅዱስ መስቀሉ ሊያርቁንና ሊለዩን የሚሹና የሚሞክሩ ቻርልስ ራስል የላካ ቸው ብዙዎች ጸላዕተ መስቀል (የመስቀል ጠላቶች) እንደ አሉና ከእነዚኽና ከመሰሎቻቸው ተጠብቀን ልንኖር እንደሚገባ ነው የመከረን ፡፡ እነርሱንም ‹‹…ብዙዎች ለክርስቶስ መስቀል ጠላቶች ኾነው ይመላለሳሉ…›› ሲል አስቀድሞ ገልጿቸዋል ፡፡ 1 ፊልጵ = 3 ÷17 ፡፡

          እኛም ኢትዮጵያውያን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ከጠቆመን ከእነዚኹ ጸላዕተ መስቀል (የመስቀል ጠላቶች) ተለይተን ከእግረ መስቀሉ ሥር ዝቅ ብለን ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ‹‹…ዕፅ ዘለከፎ ደሙ ክቡር…›› እንዳለ በጌታችንና በመድኃኒታችን በአምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ የከበረ ደሙ ፈሳሽነት ለተቀደሰው ቅዱስ መስቀሉ እንሰግዳለን ፡፡ የጌታችን ቅዱሳት እግሮቹ ከነኳቸው ቅዱሳት መመላለሻዎችና ማረፊያዎች አንዱ‹‹…ወንሰግድ ውስተ መካን ኀበ ቆመ እግረ እግ ዚእነ—የጌታችን ቅዱሳት እግሮቹ በቆሙበት እንሰግዳለን ፡፡…›› በማለት ቅዱስ ዳዊት የተናገረ ለትና ቅዱሳት የጌታ እግሮቹ ተቸንክረው የዋሉበት ይኸው ቅዱስ መስቀሉ ነውና ፡፡ መዝ = 131 ÷ 7  ፡፡

           የቀደሙ ክርስቲያን አባቶቻችን ለመስቀሉ ክብር ሲሉ እጅግ ብዙ መንፈሳዊ ተጋ ድሎን ፈጽመዋል ፡፡ ንጉሥ ሕርቃል ወደምድረ ፋርስ ዘምቶ የተዋጋው (የመስቀል ጦርነት) ፋርሳውያን ወደፋርስ ወስደውት የነበረውን መስቀሉን ለማስመለስ ነው ፡፡ በኋለኛው ዘመንም ቅዱስ መስቀሉ ተቀብሮ ከተገኘበት ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን መታነፁ መተከሉ ፤ እንዲሁም ደገኛው ካህን አውዶክስያ መራራውን የበረኃ ውኃ በመስቀል ባርኮ ወደጥዑምነት ለውጦ ለመስ ቀል በሚሰግዱ ክርስቲያን ላይ ይዘብት የነበረ ሳምራዊው ኢአማኒ ይሥሐቅን የአሳመነው በቅ ዱስ መስቀል ኃይል ነው ፡፡

         በመኾኑም በዓለም ኹሉ ከጽንፍ እስከ ጽንፍ ለክርስቶስ ፍቅር የአለንን ሕያው ተአ ምኖ የሚያስረዳ የመዳናችንን ጥልቅ ምሥጢር ጠቅሎ የያዘው ነገረ መስቀሉ የሚገለጽበት የደመራ በዓልን እኛ ኢትዮጵያውያን በጥንቃቄ ልንጠብቀው ይገባል ፡፡ በዓሉ ባለደመራ ችቦው ባለጣምራ ኾኖ በእየአደባባያችን በእየደጃፋችን ተደምሮ በርቶ በከፍታ ተነጥቆ ወጥቶ ብርሃን ሰጥቶ የአዲሱን ዓመት አዲስ ተስፋ እንደሚያሳይ ኹሉ እኛም የአለፈውን ዘመን አሮጌውን የአረጀ የአፈጀ የአመለካከታችን ጥላቻና ልዩነትን ትተን በመጭው አዲስ ዓመት ለአዲስ የፍቅ ርና የሰላም የሀገር ኹለንተናዊ አንድነት እንድንቆም ነው ነገረ መስቀሉ የሚያስተምረን ፡፡

          በእምነታዊ ተመስጦ ውስጥ በማስተዋል ወደክርስቶስ ቅዱስ መስቀሉ ስንመለከት ነገረ መስቀሉ አብዝቶ የሚያስረዳን አንድነትንና ፍቅርን ሰላምንም ነውና ፡፡ ጌታም በመሰቀሉ ላይ በአፈሰሰው ደሙ የመሠረተልን የህልውናችን ራስ የኾነውን ሰላምን ነው ፡፡ ይኽ ሰላምም ለምናምንበት ለእኛ ኢትዮጵያውያን ጥበባችንን ፤ ዕውቀታችንን ፤ ጽናችንን ፤ ድኅነተ ልዕልና ችንን የምንጐናጸፍበት ኃይላችን መኾኑን እናስተውል ፡፡

          ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶሳውያን በጻፈው መልዕክቱ ምዕራፍ ፩ ቀጥር ፲፰ ላይ ‹‹…ወነገረ መስቀሉሰ እበድ ውእቱ በኀበ ኅጕላን ፡፡ ወበኀቤነሰ ለእለ ድኅነ ኀይለ እግዚአብሔር ውእቱ—-የመስቀሉ ነገር ለሚጠፉት ሞኝነት ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነው…›› ብሎ አስተምሮናል ፡፡

          ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድም ታዲያ ከላይ የተገለጸውን በቅዱስ ዕፀ መስቀሉ የተገኘ የጌታን ማዳን በመጽሐፈ ድጓው ሲገልጽ የጌታን ቃል ጠቅሶ “ አበርህ በመስቀልየ ” ይለናል ፡፡ እስቲ የመስቀሉን ማኅሌታዊ ምልጣን ( ምስጋና ) በመጀመሪያ ቀጥሎም እስመ ለዓለሙን እንመልከት ፡፡

ምልጣን

          “ይቤሎሙ ኢየሱስ ለአይሁድ እመኑ ብየ ፡፡ ወእመኑ በአቡየ ፡፡ ዮምሰ ለእሊአየ አበርህ በመስቀልየ ፡፡ ”  

ትርጕሙ

          ጌታችንና መድኃኒታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእኔ የባሕርይ አምላክነት እመኑ ፡፡ በባሕርይ አባቴ እግዚአብሔር አብና በባሕርይ ሕይወቴ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስም እመኑ ፡፡ ለፈጠርኋቸው ወገኖቼ ፍጥረታት ኹሉ እነሆ ለድኅነተ ዓለም ከተሰቀልሁ በት ዕለት ጀምሮም በመስቀሌ የመዳን ብርሃን እሰጣቸዋለሁ ፡፡ አንድም በመስቀል ላይ በሚፈስ ሰው ክቡር ደሜ አድናቸዋለሁ ብሎ ለአይሁድ ነገራቸው ፡፡

እስመ ለዓለሙ

          “ብከ ንወግዖሙ ለኩሎሙ ፀርነ ይቤ ዳዊት በመንፈሰ ትንቢት በእንተ ዝንቱ መስቀል ዘተሰቅለ ዲቤሁ ቃለ አብ ፡፡ ወበስምከ ናኀሥሮሙ ለእለ ቆሙ ላዕሌነ ፡፡ ወካዕበ ይቤ ወወሀብኮሙ ትዕምርተ ለእለ ይፈርሑከ ከመ ያምሥጡ እምገጸ ቅስት ወይድኀኑ ፍቁራኒከ ፡፡ ወንሕነኒ ንትፈሣሕ ዮም ወንግበር በዓለ በዛቲ ዕለት በዓለ እግዚእነ ፡፡ ” 

                              ትርጕሙ

          ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት አካላዊ ቃል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለተሰቀ ለበት ቅዱስ መስቀል አቤቱ ጌታ ሆይ እኛም ከዚኽ ቀደም በአንተ አምነን ጠላቶቻችንን ድል እንነሣለን ፡፡ በጠላትነት የተነሡብን ጠላቶቻችንም ድል ነሥተን እናሳፍራቸውለን ብሎ አስቀ ድሞ ተነበየ ፡፡ ዳግመኛም ለሚፈሩሕ ለሚያመልኩህ ኹሉ ከመከራ ሥጋ ከመከራ ነፍስ አን ድም ከፀብዐ አጋንንት ይድኑ ዘንድ ለድኅነተ ሥጋ ወነፍስ የሚኾን ትዕምርተ መስቀልህን ሰጠ ኻቸው ብሎ በትንቢቱ ተናግሯል ፡፡ እኛም ( ኢትዮጵያውያን ) ዛሬ በዚኽች ዕለት የጌታችን መድኃኒታችን አምላካቸን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀሉ የአደረገልንን አምላካዊ ማዳን እያሰብን ፍጹም ደስታን እናድርግ ፡፡

ተጻፈ

ከጌቴ ገሞራው

አዲስ አበባ—-ኢትዮጵያ

2012 ዓመተ ምሕረት

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *