“አዋ አእመረ”
ከጌቴ ገሞራው
ዋድሌያዊው ወዋሸሬያዊው
“ወይ የዘንድሮ ክረምት እጃ እንጃ እትት…ትት ኹኹ አቤት አቤት ቁር” አለና የታጠፈ ጉልበቱን ዘርግቶ ተንጠራራ ፡፡ ተንጠራርቶ መለስ ሲል ዕልፍ አዕላፍ የመርፌ ውስውስ የተመላለሰበት ጥቁር ድሪቶው ጠረር ሲል ሰማ…
ወደታች ሲመለከት ሰፊ ትልቅ አውራ ጣቱን ተከትሎ የሾለከ ጭቅቅታም እግሩ አፈጠጠበት ፡፡ ተገላበጠና እንደ መስኮት ሁሉ የጎጆይቱን ምርጊት ቀርፎ በሰራው ሸንቁር እጮልጎ እዳሪውን ተመለከተ ምን ጅል ቀን ነው አያ! አቤት ሲቀር…፡፡
ዛሬን ድርዳሮው እንጨት ክንድ ተሰንዝሮ እየተለካ በሁለት ወልጋዳ ባላ ላይ ተደግፎ ከግርግዳው ጋራ በሐረግ ልጥ ከተተበተበው የእንጨት ቆጥ አልጋው ላይ ተኝቶ ቢውል ምንኛ በወደደ….
ግና ማታ ተቅጸላ በኋላ የሚቀመስ ነገር ወይ አንዲት ምንም የለም ፡፡ እርግጥ ባለፈው ወርኃ ጽጌ ከደብር ደብር ከመንደር መንደር ዞሮ የሰበሰበውን ኮቸሮ በትንሽ ማድጋ አኑሯል ፡፡
እርሱም ቢሆን ግን ከወዲሁ እንዲያ ካሉት ነሐሴና መስከረምን የሚያወላዳ አይኾንም በምድረ ጨጎዴ በተለመደው የኑሮ ዘይቤ ደግሞ ለተማሪ ረኃቡ ለገበሬ ችግሩ የሚጸናው በእኒኽ ኹለት ወራት ነው ፡፡ ምን ይሻላል ምን ላድርግ ሲል አሰበ ፡፡
ስለወርኃ ክረምቱ ጽናትና የዕለት ጉርሱን እንደዴተ እንደሚያደርግ አስቦ ተጨነቀ ፡፡ ተጨንቆ አዘነ ፡፡ አዝኖ ተከዘ ፡፡ እናም በጨጎዴ ላይ አጕረመረመ ፡፡ “ አይ ጨጉዶ ጨጉዴ ደብርነ ደብረ ምንዳቤ አለ ተማሪ” አለና በዚያች የጎጆይቱ ትንሽ የግድግዳ ሽንቁር አጨልጎ እንደገና በዐይነ ትካዝ ጨጎዴን ይመከታት ገባ….
ጨጎዴ ደግሞ ችፍችፍ የሚለውን ዝናም እየተቀበለች አኩርፋለች ፡፡ አይ ጨጎዴ መቸም መች አይጠዳሽ ናት ፡፡ ጨጎዴ ሀገረ-ጉም…ሀገረ ነፋስ…ሀገረ ቍር…ነገር ግን የዋድላው…የዋሸራው…የጎንጁ ውብ ቅኔ መፍለቂያ ሀገረ- ምሥጢር ፡፡ ከቶ ጨጎዴን የማያው ቃት ይኖር ይኾን….ማንም የለም ፡፡ ማን አለና !!….ከነቍር ምንዳቤዋና ከነውብ ቅኔዋ ጭምር….ጨጎዴን….
ጨጎዴ የምትገኘው በጎጃም ክፍለ ሀገር ከልጅ አንበራ በላይ ፈንገጣ ማርያምን በሩቅ እያስተዋለች…ከአዳማ ተራራ ሥር…ከአዳማ ጉያ ተሸጉጣ ነው ፡፡ ከበላይዋ ደግሞ ጀርባውን ለአዴት ሰጥቶ ወደታች በሚያያቸው ልጅ አንበራ…ዝጉዳ…ጉሌ…ዳቢትና ቋሪት ላይ ደረቱን ነፍቶ የቆመው የአዳማ ተራራ ከማዶ ሲያስተውሉት ጨጎዴን በእቅፉ አግብቶ እሽሩሩ የሚል ይመስላል ፡፡
ግን እንደ ደብረ ታቦር ተራራ ሰማይ ጥግ የደረሰ አንዳች አገር የሚያህል ተራራ አዳማ የተባለው መች ይኾን…ምድረ- ገነት ሳትሠራ…!?…አብሕርት ቀላያት ሳይፈጠሩ አስቀድ በፍጹም አይኾንም ፡፡ ታዲያ መቼ እንጃ ማን ያውቃል ፡፡ እርሱ እንደሁ አይናገር አይጋገር..!!… ምን ቸገረኝ ብሎ ፡፡ አዳማ ተብሏል አዳማ ፡፡ በቃ ፡፡ አለቀ ፡፡
የአዋ አእመረ የልመና ምድቡ አዳማ ነው ፡፡ ከአዳማ ግርጌ የአዳማን ተረተር እየተ ከተለ ከሠፈረው ችምችም መንደር ሲደርስ ወደግራ ታጥፎ ልመናውን ይጀምራል ፡፡ ከተኛበት ቀና አለና ድሪቶውን ወደታች ገፍቶ ተነሣ ፡፡ የቈጥ አልጋውን የባላ ጕጥ በዝግታ እየረገጠ ወርዶ ቆመ ፡፡ የተኛበትን ደበሎውን አንስቶ ደረበው ፡፡ አቤት ሲሞቅ !!…
እንደመልካም ካባ የቀን ልብስ የለት ምንጣፍነቱ ደኅና ጠቅሞታል ፡፡ ደበሎ ውስጥ ቡቱቶ አቡጀዲውን ለበሰና አኩፋዳውን ከሰቀለበት አውርዶ ተመለከታት ፡፡ እንደ እርሱ ሆድ ባዶ ኾናለች…ምስኪን…ይችኑ ባዶ አኩፋዳውን አፏን ወደታች ዘቅዝቆ ግራና ቀኝ መታ መታ አደረገና…አራግፎ…በግራ ክንዱ ካንጠለጠላት በኋላ…ብትሩን ይዞ ከትከሻው ጀምሮ ወደምድር ጎንበስ ብሎ በጠባቧ በር የጎንዮሽ ሾልኮ ወጣ ፡፡
መዝጋት አያስፈልግም ፡፡ ውትርትሩን የተማሪ ጎጆውን በር ሳብ አድርጎት ብቻ ትቶት አዘገመ ፡፡ እያዘገመ ከእርሱ ሌላ ሌላ መንደር…ሌላ ተራራ…ሌላ ሀገር…የሌለ ይመስል እንዲያ ሰፍቶና በዝቶ ጐልቶና ገዝፎ ከጨጎዴ…ከፈንገጣ…ከሐተታ ማርያም…ከልጅ አንበራ …ከአዴት…በላይ በስተቀኙ የተገማሸረውን የዕለት ጉርስ የሚያገኝበትን አስፈሪውንና ጮቄያማውን የአዳማ ተራራ ተመለከተው ፡፡
አዳማ ደግሞ በግርማ ተመልቶ ኹሉን ወደታች ቀልቁል እያየ ተኮፍሷል ፡፡ እንደ ልማዱም በጉም ካባው ተሸፍኖ አሮጌ ቄስ መስሏል ፡፡ ጽኑው ክረምት እጅግ ጸንቶበት ያስከፋው ይመስላል ፡፡ ከፍቶታል ፡፡ አዋ አእመረም እንደ አዳማ ተራራ እየከፋው ሸጥ ለሸጥ በሚወስደው ሠርጥ መንገድ ከእግሩ ነጠቅ ነጠቅ እያለ ያዘግም ጀመር…
ይቀጥላል…..
ተጻፈ
በወርኃ መስከረም 10 ቀን 2012 ዓመተ ምሕረት
አዲስ አበባ—–ኢትዮጵያ