ከጌቴ ገሞራ
ዘዋድላ ወዘዋሸራ
አምጻኤ ዓለማት ገባሬ መላዕክት ልዑል እግዚአብሔር ቅዱሳን መላዕክትን በነገድ መቶ በከተማ ዐሥር አድርጎ ፈጥሯቸዋል ፡፡ የእሊኽ ቅዱሳን መላዕክት ተፈጥሮ ዋነኛ ዓላማም እርሱ ፈጣሪያቸው ሕያው እግዚአብሔርን ያመስግኑ ዘንድ ሲኾን ዳግመኛም ስለፍጥረተ ዓለም ኹሉ መዳንና ይለምኑ ዘንድ ነው ፡፡ ኢሳ = 6÷3 ፡፡ ሪእ 5÷11 ፡፡ ዕብ = 1÷14 ፡፡ ማቴ = 8÷10 ፡፡
ነገር ግን የቅዱሳን መላዕክት ተልዕኮተግብር ይኽ ብቻ አይደለም ፡፡ ይልቁንም የኹላቸውም ቅዱሳን ጻድቃን ጸሎት ወደ ልዑል እግዚአብሔር መንበረ ፀባዖት የሚደ ርሰው በእሊኽ ቅዱሳን መላዕክት አዕራጊነት መኾኑን ቅዱሳት መፃሕፍት ይመሠክሩልናል ፡፡ ብእሴ ራእይ ጻድቅ ሔኖክ ይኽንኑ ሲያብራራ “…ወበህየ ” ብሎ ዓለመ መላዕክትን ከገለጸ በኋላ “….ርእያ አዕይንትየ ማኅደሪሆሙ ለጻድቃን ምስለ መላዕክት ይስእሉ ወያስተበቊዑ ወይጼልዩ በእንተ ውሉደ ሰብእ ፡፡ ወጽድቅሰ ከመ ማይ ይውኅዝ በቅድሜሆሙ ፡፡ ወምሕረት ከመ ጠል ውስተ ምድር…” በማለት ተናግሯል ፡፡ ኄኖ = 9 ÷ 28 ፡፡
ትርጉሙም “…በዚያ ቅዱሳን ጻድቃን ከቅዱሳን መላዕክት ጋራ የሚኖሩበትን ዐይኖቼ አይተዋል ፡፡ ለሰው ልጆችም ይለምናሉ ፡፡ ይማልዳሉ ፡፡ ይጸልያሉ ፡፡ ቸርነት በፊታ ቸው እንደ ውኃ ይፈስሳል ፡፡ ምሕረትም በዚኽ ዓለም ይለመልማል ፡፡ አንድም ቸርነት በዝቶ ይሰጣል ፡፡ ምሕረትም ይትረፈረፋል ” ማለቱን እንመለከታለን ፡፡
ነባቤ መለኮት ወንጌላዊ ቅዱስ ዮሐንስም በመጽሐፈ ራእዩ “ የወርቅ ጥና ይዞ በታቦቱ ፊት ለቆመው መልዐክ ለቅዱሳን ኹሉ ጸሎት እንዲጨምረው ብዙ ዕጣን ተሰጠው ፡፡ የዕጣኑም ጢስ ከቅዱሳን ጸሎት ጋራ ከመልዐኩ እጅ ወደ እግዚአብሔር ዐረገ …” ሲል ይነግረናል ፡፡ ራእ = 8÷3 ፡፡
እንግዲህ ከዚህ በላይ ከብዙ በጥቂቱ በተገለጸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ መሠረት የቅዱሳን መላዕክትን ኩነት ተፈጥሮና ተልዕኮተ ግብር ስንረዳ ፈጣሪያቸው ልዑል እግዚአብሔር በፊቱ ይቆሙ ዘንድ የመላዕክቱ ኹሉ አለቆች አድርጎ የሾማቸው ሰባት ሊቃነ መላዕክት አሉ ፡፡ ከእሊኽም አንዱ “ ዘሣልሳይ ማዕረጊሁ “ የተሰኘ ከቅዱስ ሚካኤልና ከቅዱስ ገብርኤል ቀጥሎ የተሾመ ተዐምረኛው መልዐክ ፈታሔ ማሕፀን ሊቀ መላዕክት ቅዱስ ሩፋኤል ነው ፡፡
በእርግጥ ነቢዩ ኄኖክ “….ኹለተኛው መልዐክ ፣ በሰው ልጆችም ቊስልና በበሽታ ኹሉ ላይ የተሾመ ቅዱስ ሩፋኤል ነው…” በማለት የሊቀመላዕክት ቅዱስ ሩፋ ኤልን ማዕረገ ሢመት ከሦስተኛ ወደኹለተኛ ማዕረገ ሉዓሌ ከፍ አድርጎ ገልጾ ይኽ ንንም የነገረው መጋቤ ድንግል ሊቀ መላዕክት ቅዱስ ፋኑኤል እንደኾነ ጽፏል ፡፡ ኄኖክ = 10 ፣ 11÷14 ፡፡
መጽሐፈ አክሲማሮስም “ … ወለፆታ ዐሠርቱ ስሞሙ መናብርት ወሊ ቆሙ ቅዱስ ሩፋኤል ፡፡ ወእሉ እሙንቱ እለ ይቀልል ሩፀቶሙ እምነፋስ ወነድ ለእለ ይፀውሩ ወላትወ መብረቅ ወኵናተ እሳት ዘይነድድ ፡፡ ወአንበሮሙ በዳግሚት ሰማይ ፡፡ ወእምዝ ነሥአ እምሠራዊተ ሩፋኤል ፳ወ፬ተ ሊቃናተ ፡፡ ወአቀሞሙ ዐውደ መንበሩ …” ይላል ፡፡
ትርጉሙም “ ዐሥሩም ነገድ ስማቸውን መናብርት አላቸው ፡፡ አለቃቸ ውም ቅዱስ ሩፋኤል ነው ፡፡ እሊኽም የመብረቅ ጋሻ የእሳት ጦር ይዘው ከእሳትና ከነፋስ ይልቅ የሚፋጠኑ ናቸው ፡፡ እሊኽንም በረኃማ በኹለተኛው ከተማ አኖራቸው ፡፡ ከሠራዊተ ሩፋኤልም ኻያ አራቱን ሊቃናት መርጦ በመንበረ ስብሐቱ ዙሪያ አቆማ ቸው…” ማለት ነው ፡፡ ይኽ የእሳታውያን መናብርት አለቃ ሊቀመላዕክት ፈታሔ ማሕ ፀን ቅዱስ ሩፋኤል ከላይ በተገለጸው መሠረት የሰውን ልጆች ይረዳ ይታደግ ዘንድ ከፈጣሪው ዘንድ ብዙ ማዕርጋተ ሢመት ተሰጥተውታልና ፡፡
እሊኽም ፈታሔ ማሕፀን ፣ ዐቃቤ ኈኅት ፣ ሰዳዴ አጋንንት ፣ ከሣቴ ዕው ራን ፣ ፈዋሴ ዱያን ፣ ፈታሔ ጸጋ ወሀብት የተሰኙት የሊቀመላዕክት ፈታሔ ማሕ ፀን ቅዱስ ሩፋኤል ስሞቹ በፈጣን ምልጃው ከፈጣሪው ለሰው ልጆች የሚያሰጣቸው የተል ዕኮታዊ ግብረ አድኅኖቱ መገለጫዎች መኾናቸውን ልብ ይሏል፡፡
“ ሩፋኤል” የሚለው የስሙ ትርጓሜም ስንኳ የሚያስረዳው ይኽንኑ ነው ፡፡ “ ሩፋ” ማለት ጤና ፣ ፈውስ ማለት ሲኾን “ ኤል” ማለት ደግሞ ጌታ ፣ አምላክ ፣ እግዚአብሔር ማለት ነው ፡፡ በተጨማሪም ታላቁ ሊቀ መላዕክት ቅዱስ ሩፋኤል በከበረ መጽሐፈ ድርሳኑ ውስጥ “ ስምየሂ መድምም ፡፡ ወትርጓሜሁ ፈውሰ አምላክ” በማለት ስሙንና የስሙን ድንቅ ትርጓሜ እንደገለጸልን እናስታውሳለን ፡፡
እንግዲህ “ ሩፋኤል “ ማለት ከእግዚአብሔር አምላክ ለሰው ልጆች መጠ በቅ የተሰጠ ጤና ፈውስ ወይንም ፈውሰ እግዚአብሔር ማለት መኾኑን ልብ ይሏል ፡፡ በተጨማሪ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በመልዕክቱ «…አንድ አንዶች ቅዱሳን መላዕክትን በእንግድነት ተቀብለዋል…» እንዳለውም ከሰባቱ ሊቃነ መላዕክት አንዱ የኾነ ቅዱስ ሩፋኤልን በእንግድነትና በረዳትነት ከተቀበሉ ሰዎች መኻል ደጉ አረጋዊ ጻድቅ ጦቢት በታላቁ ቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ እናገኘዋለን ፡፡ ዘፍ = 19÷2 ፡፡ ጦቢ = 3÷12 17 ፡፡ ዕብ = 13÷1 ፡፡
በንጉሠ ፋርስ ስልምናሶር ዘመን ከቄድዮስ አውራጃ ታቢስ ወደፋርስ ነነዌ የተማረከው ንፍታሌማዊው የገባኤል ልጅ ጻድቅ ጦቢት «…በተገቢው እውነተኛ ሥራ ጸንቼ ኖርሁ ፡፡ እኅሌን ለተራቡ ልብሴንም ለተራቈቱ ድኾች ሰጠሁ ፡፡ በየአደባባዩ በጨ ካኙ ሰናክሬም እጅ በጊዜው ተገድለው የተጣሉ ሰዎችንም እያነሣሁ እቀብር ነበር…» በማለት በአምላኩ እግዚአብሔር ፊት ስለ ጽድቅ ብሎ የአደረገውን የበጎ ምግባር ተጋድሎ ዘርዝሮ ገልጾልናል ፡፡
በፋርስ ነነዌ ውስጥ የነበሩ ሰዎች ግን “… እንዴት ሰናክሬምን ያህል ንጉሥ ጠልቶ የሚገድላቸው ሰዎችን እያነሣ ይቀብራል !!….” እያሉ ንፍታሌማዊው የገባኤል ልጅ ጻድቅ ጦቢትን ያሙት ነበር ፡፡ እንደውም በንጉሡ ፊት በሐሰት ወንጅ ለው ሊገሉት በፈለጉ ጊዜ ጦቢት 55 ቀን ሙሉ ከቤቱ ሳይወጣ ተሸሽጎ ቆየ ፡፡
እንግዳ ሳይዝ የማይመገበው ደጉ ሰው ጦቢት አንድ ቀን ግን «…እስኪ የተራበ ድኻ ከአገኘህ ከመንገድ ይዘህ ና…» ብሎ ልጁ ጦቢያን ወደአደባባዩ ሥፍራ ላከው ፡፡ «…ልጁም የሞተ አንድ ሰው በአደባባዩ ወድቋል…» የሚል አሳዛኝ መልስ ነገረው ፡፡ ጦቢት አልዘገየም ፡፡ የቀረበለትን ምግብ ትቶ ፤ ከቤቱ ወጥቶ ፤ የሞተውን ቀብሮ ፣ ዕድሞው ሥር ተኝቶ ሳለ ዕድሞው (ጣራው) ላይ ከነበሩት ወፎች ዐይኑ ላይ በዐረፈበት ትኩስ መርዘኛ ኵስ የዐይኑን ብርሃን አጣ ፡፡ ኑሮው ጨለመበት ፡፡ የዕለት ምግቡን ስንኳ የሚያገኝው ከወንድሙ አናሔል ልጅ አኪአኪሮስ እጅ እየተለገሠ ነበር ፡፡
ኾኖም ጻድቁ ጦቢት ተስፋ አልቈረጠም ፡፡ ተስፋ አልባ የነበረችው ሚስቱ ሐናም “ ጸሎትህና ምጽዋትህን ምን ጠቀመህ “ እያለች ብትዘብትበትም ዘወትር በልቡ እያዘነ እንባውን በማፍሰስ ወደ እግዚአብሔር ይለምን ነበር ፡፡ በዚያ የችግሩ ወራት ነበር በሜዶን አውራጃ ራጊዝ ከሚኖረው ገባኤል ዘንድ ቀድሞ በአደራ ያስቀመጠውን ገንዘብ እንዲያመጣለት ልጁ ጦቢያን የአዘዘው ፡፡
ልጁ ጦቢያም «…አባቴ ሆይ ያዘዝኸኝን እሠራለሁ ፡፡ ነገር ግን ሀገሩን አላውቀውምና እንዴት ብቻዬን ልሔድ እችላለሁ…» በማለት አብሮት የሚሔድ ሰው ሲፈልግ ከመንገድ ላይ ሊቀመላዕክት ቅዱስ ሩፋኤልን አገኘው ፡፡ ኾኖም መልዐክ እንደኾነ አልተረዳም ነበር ፡፡ ወደ አባቱ ጦቢት ዘንድ ይዞት መጣ ፡፡
የእሳታውያን መናብርት አለቃ ሊቀ መላዕክት ፈታሔ ማሕፀን ቅዱስ ሩፋኤልም «…እኔ የታላቅ ወንድምህ ዘመድ አዛርያ ነኝ…» ሲል ጦቢትን ተዋወቀው ፡፡ ስለ ጕዞው ዋጋ ተነጋገሩ ፡፡ ተስማሙ ፡፡ ጦቢትም ልጁ ጦቢያን «…ከዚህ ሰው ጋራ ሒድ ፡፡ እግዚአብሔር ጎዳናችሁን ያቃናላችሁ ፡፡ መልዐኩም አብሯችሁ ይሒድ…» አለው ፡፡ ኹለቱም ወጥተው ሔዱ ፡፡
በመንገዳቸውም ሲሔዱ ምሽት ላይ ወደ ጤግሮስ ወንዝ ደረሱ ፡፡ ጦቢያም ሊታጠብ ወደ ወንዙ በቀረበ ጊዜ ታላቅ ዓሣ ከውኃው ውስጥ ወጥቶ ወደ እርሱ ተወረወረበት ፡፡ መልዐኩም «…ፍጠን ዓሣውን ይዘህ እረደው ፡፡ ጉበቱንና ልቡን ሐሞቱንም ይዘህ ለይተህ አስረህ ያዝ…» አለው ፡፡ ስሙን “ አዛርያ “ ብሎ የተገለጸው ቅዱስ ሩፋኤልና ጦቢያም ወደ ራጊስ በደረሱ ጊዜ በጻድቅ ራጉኤል ቤት ያድሩ ዘንድ ገቡ ፡፡ የራጉኤል ልጅ ሣራም ተቀብላ ደስ አሰኘቻቸው ፡፡ መልዐኩ ቅዱስ ሩፋኤልም የጕዞው አጋር የትዳሩ መካር ኾኖት ጦቢያን ሣራን ያገባት ዘንድ ረዳው ፡፡
በእርግጥ በጣኒስ ተወላጇ የራጉኤል ልጅ የኾነችው ሣራ ቀድሞ ለ7 ሰዎች በእየጊዜው ብትታጭም ሰባቱንም ወንዶች አስማንድዮስ የተባለ ክፉ ቊራኛ ጋኔን ገድሎባታል ፡፡ በዚህ ምክንያትም የአባቷ አገልጋዮች ሳይቀሩ ቢያሸሟጥጧት ሰዎችም ኹሉ ከማኅበራዊ ኑሮ ቢያገሏትም እርሷ ግን «…አቤቱ አምላኬ ሆይ ሰውነቴን ለአንተ ሰጠሁ ፡፡ እባክህ በዐይነ ምህረትህ ተመልከተኘ…» እያለች ወደ ፈጣሪዋ ልዑል እግዚአብሔር ትማፀን ጀመር ፡፡
ስለዚህም የሠራዊት ጌታ ልዑል እግዚአብሔር ሊቀመላዕክት ቅዱስ ሩፋኤልንም መጀመሪያ ወደጦቢት ዘንድ ልኮ ከጦቢያ ጋራ አብሮት እንዲጓዝ ፤ ክፉ ጋኔን አስማንድዮስንም ከወለተ ራጉኤል ሣራ በማስወገድ ለጦቢያ ሚስት አድርጎ እንዲድርለት ወደነነዌም ሲመለሱ የጻድቅ ሰው ጦቢት ዑረተ ዐይኑን (የዐይኑን ብልዝ) ይፈውሰው ዘንድ የላከው ፡፡
የአረጋዊ ጻድቅ ሰው ጦቢት ልጅ ጦቢያም አብሮት የሚጓዘው ቅዱስ ሩፋኤል በመንገድ ላይ ሳሉ የነገረው ወደ ሣራ በገባ ጊዜ ከደቀቀ ዕጣን ጋራ የዓሣውን ጉበትና ልቡን አጨሰው ፡፡ ጋኔኑም በዕጣኑ መዓዛ ሸሽቶ ወጣ ፡፡ ቅዱስ ሩፋኤልም በእሳት ሠንሠለት አስሮ አጋዘው ፡፡ በራጉኤልና ዕድና ቤት የጦቢያንና የሣራን ጋብቻ ከአስፈጸመ ዐሥራ ስድስት ቀናት በኋላም ወደ ነነዌ ሲመለሱ ጦቢያ የያዘውን የዓሣውን ሐሞት የአባቱ ጦቢትን ዐይን እንዲቀባው አድርጎ የወዳጁን ጦቢት ዐይን ፈውሶታል ፡፡
«…የቅዱሳንን ጸሎት ከሚያሳርጉ ሰባቱ ሊቃነ መልዐክት አንዱ እኔ ሩፋኤል ነኝ…» ሲል በመጨረሻ ጊዜ ለእነ ጦቢት ሰማያዊነቱን የገለጸላቸው ቅዱስ ሩፋኤል በሀገረ ቊስጥንጥንያም ተገልጾ ድንቅ ገቢረ ተዐምራቱን አሳይቷል ፡፡ በአማላጅነቱ ታምነው በሥዕሉ ፊት የተማፀኑ ቴዎድዮስዮንና ዲዮናስዮስን ለነጋሢነትና ለጵጵስና መንበረ ክብር አብቅቷቸዋል ፡፡ በስሙ የታነፀች ቅድስት ቤተክርስቲያንን ለመ ዝረፍ የመጡ ወንበዴዎችን ሳይቀር የተመዘዘ ሰይፍ ይዞ በመገለጽ ገሥጿቸዋል ፡፡ ጦቢት = 12÷15 ፡፡ 2ኛ ዜና መዋ = 21÷16 ፡፡ መሳ=13÷3 ፡፡
ዳግመኛም በጌታችንና መድኃኒታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትእዛዝ ለአባቶቻ ችን ቅዱሳን ሐዋርያት «…የሰማያት መዛግብትን እከፍታቸውም እዘጋቸውም ዘንድ ከእጄ በታች ተጠብቀው እንዲኖሩ ሥልጣን ተሰጥቶኛል ፡፡ በስሜም በጎ ነገር የሚያደርገውን እኔ በመከራው በችግሩ ጊዜ ኹሉ እራዳዋለሁ ፡፡ በበዓሌ ቀንም ስለስሜ የሚዘክርና የሚመጸውት ሰውን ወደ ሰማያዊት ኢየሩሳሌም በሠረገላ ብርሃን አደርሰዋለሁ ፡፡ በሰማያዊ መዓዛም ደስ አሰ ኝዋለሁ…» ብሎ ከፈጣሪው የተሰጠውን ቃል ኪዳን ነግሯቸዋል ፡፡
ስለዚኽ በአምላኩ እግዚአብሔር ትእዛዝ አዛርያ ተሰኝቶ በሰው አምሳል ወደ ጦቢት መጥቶ ጦብያን ረድቶ ከወለተ ራጉኤል ክፉ ጋኔን አስማንድዮስን ለይቶ ጻድቅ ጦቢትን ከዑረተ ዐይን የፈወሰ የአዳነ ስሙን ለሚጠሩት የፈጠነ የሊቀ መላዕክት ፈታሔ ማሕፀን ቅዱስ ሩፋኤል ቃል ኪዳኑን ተስፋ አድርገን በአማላጅነቱ ታምነን ለምንኖር ወዳጆቹ ኹሉ በላያችን እንደአንበሳ እያገሣ የሚሸምቅብን ክፉ ጠላት ዲያብሎስን አርቆ ዑረተ ኃጢአታችንን አስወግዶ ብርሃነ ረድኤቱን የጐናጽፈን ፡፡ ሀብተ ጸጋውን አብዝቶም ከክፉ ኹሉ ይጠብቀን አሜን ፡፡
ተጻፈ
በወርኃ ጳጕሜን 3 2011 ዓመተ ምሕረት
አዲስ አበባ—–ኢትዮጵያ