“ሹክሹክታ”
ከጌቴ ገሞራው
ዘእምዋድላ ወዋሸራ

“አልኈሰሰ = ሹክ ሹክ አለ” የሚለውን ግሥ በማንሣት— የግሡን አርባ ተከትለን ብንጓዝ ስተት አድጋ ወስዶ…«ለኈሳስ” ከሚለው ከራሱ ዘርእ ያደርሰናል… ኾኖም “ “አልኈሲሶ በእዝና…” የሚለውን ብሂለ ድጓ ስንመለከት ቀረብ ብሎ በዝግታ በሥርዓት በፍር ሐት በአክብሮት በትሕትና የተነገረ የምሥራች የደስታ የበጎ ቃል ያለው ትርጓሜ መኾኑን እንረዳለን…
ነገር ግን ጉባኤ ቤት የዋሉ ምሥጢር የአደላደሉ ሊቃውንት ከግእዝ ቋንቋ የተወለ ደው የአማረኛን ቋንቋ በሦስት ዐይነት ከፍለው ይናገሩለታል ፡፡ የቤተ ክህነት ፤ የቤተ መንግሥት ፤ የሕዝብ ብለው ነው ፡፡ እናም “ ሹክሹክታ ” የሚለውን ቃል በሕዝባዊ (ምእመ ናዊ) ፍቺው ስንጨምቀው “ሹክሹክታ” ማለት በአብዛኛው አንዱ ስለሌላው የሚያወራው… የሚያወጋው እውነት…ሐሰት…ሽሙጥ…ሥላቅ የሚተላለፍበት ሲኾን ሐሜታዊ ፍኖተ ዘርቅነት ይጐለብትበታል ፡፡
አብዛኛው የ“አልኈሰሰ = ሹክ ሹክ አለ” ትርጓሜያዊ ስሜት ይኼው ነው ፡፡ ምክን ያቱም ለሐሜቱ ርኵስ “ሹክሹክታ” መጽሐፈ መዝሙር ተስማሚ ቃል ይሰጠናል፡፡ “ጽሚት” ይለዋል…፡፡ ይኹንና “ጽሚት” የሚለውንም ሥውር…ዝግታ… ጸጥታ….ቀስታ እያሉ መተር ጉም ይቻል ይኾናል…ነገር ግን ሥውርም ይበል ዝግታ…. ጸጥታም ይበል ቀስታ…. “ጸሚት” ስንል ያው እንግዲህ “ሹክሹክታ”…. ማለታችን ነው… አየደል እንዴ!… ነው እንጂ…
“ ዘየሐሚ ቢፆ በጽሚት…” አይደል የሚለው መጽሐፉ ;… የኹሉ ፍጻሜ… የኹሉ ቀዳሚ ጥንት መጀመሪያ የኾነው ቅዱስ መጽሐፍ እንዲህ ካለ ደግሞ “ሹክሹክታ” ጥንትም ነበር… ዛሬም አለ…. አመ ከመዮም… እንደዛሬው ወደፊትም ይኖራል ማለት ነው ፡፡
አንባቤ ሆይ !! “ሹክሹክታ” እንዴት ይፈጠራል ; ትለኝ ይሆናል…. በዝግታ ይፈጠራል ፡፡ በዝግታ ይካኼዳል ፡፡ በዝግታ ይከናወናል ፡፡ አስተውል ባልደረባቸ ውን…ወንድማቸውን… ጓደኛቸውን… ወገናቸውን…አንተን… እኔን… እሱን… እሷን … እሳቸውን… በሹክሹክታ የሚያሙ መቼም መች አይቀሬ ነው ይኖራሉ ፡፡ ለምን ; አትበለኝ ግን ለምን ; ማለት የዋህነት ነው…
ምክንያቱም ጸጋህ… ሞገስህ… ጥረትህ ቅንነትህ ባለሙያነትህ…. ለታላቅ ክበር መመረ ጥህ መጠራትህ… ይኼ ወይም ሌላው ስጦታህ…. ጥቂቶችን ደስ አያሰኛቸው ይኾናል… ምን ታደርገዋለህ ; ሰዎች ሲባሉ እንዲህ ናቸው… እና እናማ ወደድህም ጠላህ የ”ሹክሹክታ” መነሻው ቅንዐት ነው…
ደግነቱ ሐሜትን በ”ሹክሹክታ” የማሽሞንሞን ከፍተኛ ልምድ ያላቸው የጥቂት ሐሜተኞችን ልብ ብለህ ተከታትለኻል ; … ከአንዲት ነገር በቀር ምንም ያላቸው ባዶ ናቸው… በዚያ ላይ ፈሪዎች ናቸው… ድንጉጦች…. አይገርምም ; በቃ ምንም ይኹን ምን ፊት ለፊት አያወሩም…. ለሚያሠሩበት መረጃ… ለሚያሙበት ማስረጃ ያላቸውማ !… የላቸውም ፡፡ … አይ የሰው ነገር ! እንደው ብቻ በቅንዐት… እንደው ብቻ “በሹክሹክታ” መብከንከን ነው አይገርምም !…
ሰማኒያ ወአሐዱ መጽሐፍ ቅዱስና ቅዱሳት አዋልድ መጻሕፍት በአንድነት መክረው ዘክረው በአንድ ቃል መጀመሪያ ”ሹክሹክታን” የቋጠራት… ዲያብሎስ ነው ይሉናል… እውነት ነው ፡፡ ይኼ አቡሃ ለሐሰት ክፉ ፍጡር ቅቤ ምላስ… “ዓይኖቻችሁ ተከፍተው … ክፉና መልካሙን የምታውቁ እንድትሆኑ ስለሚያውቅ ነው አትበሉ ያላችሁ” በማለት ነበር በርኩስ ሹክሹክታው ገነትን ያህል ቦታ… እግዚአብሔርን ያህል ጌታ እነአዳምን ያሳጣቸው ፡፡
እየውልህ አሁን “ለምን ; በለኝ… አየህ አሁን ለምን ; ማለት ብልህነት ይሆናል፡፡ እርሱ በትዕቢት… እርሱ በድፍረት ያጣውን ቦታ አዳም ያዘዋ !… ያዘበት !… መሐሪው አምላክ ሲምረው ዲያብሎስ ባለመማሩ…ወደቀ…. አዳም ግን ከበረ… ገነት ገባ… ገነትን ወረሰ…
አዎ አዳም በገነት ቤተ መቅደስ ሆኖ የፈጠረው አምላኩን ማወደሱ መቀደሱ… ለዲያብ ሎስ የእግር እሳት ሆነበት… የሚገርመው ዛሬም ዲያብሎስ አላረፈም ማለት ነው… ምክንያ ቱም ቅንዐትን በአንዱ ሕሊና ፀንሶ ያድርና አንዱን በአንዱ “ሹክሹክታ” ሊያማው ሲያሳማው ይኖራላ !…ይኖራል…
በነገራችን ላይ ይህ የዘመን መለወጫ ወርኃ መስከረም “ሹክሹክታ” የነገሠበት ነው እንበል ይሆን;… እንዴት;… “ አትሉኝም… በአባታችን በእስክንድርያው ሊቀጳጳሳት ዘብፁዕ አባ ድሜጥሮስ ላይ የደረሰውን “ሹክሹክታ” ያስታውሰናላ !… አባ ድሜጥሮስ ጌታ በዐረገ በ)V ዘመን ሊቀ ጳጳሳነትን በተሾመ በ08 ዓመቱ መንፈስ ቅዱስ መጽሐፈ ሓሳብን የገለጸለት ቅዱስ አባት ነው…
… ነገር ከሥሩ ውኃ ከጥሩ እንዲሁ “አርማስቆስ ደማስቆስ የሚባሉ ኹለት ወንድማ ማች ነበሩ…በረኃብ ምክንያት ብሔር ሞዓብ ተሰደዱ… ሚጠት ሳይደርስ /ሳይመለሱ/ የልዕልተ ወይን አባት ሞተ… ከአጓቷ ቤት ከድሜጥሮስ ጋር አብረው አደጉ…”
አይገርምም ; ኹለት ወጣቶች አካለ መጠን ሲያደርሱ… ዘመኑ ከአሕዛብ የበዙበት… ምእመናን ያነሡበት ዘመን ነበርና “ሕገ ነፍስ ኪፈርስ ሕገ ሥጋ ይፍረስ” ብለው አጋቧቸው… ከዚህ በኋላ ሥርአተ መርዓዊ ወመርዓት ያድርሱ ብለው…. መጋረጃ ጋርደውባቸው … ቤት ዘግተውባቸው…. ወጡ….
ልዕለተ ወይንም ይህን ጊዜ “ወንድሜ” አለችው ድሜጥሮስን ፡፡ “ወንድሜ !… ይህን ነገር ያሰብከው እኔን ንቀህ ነው ; ወይስ ተጠምደውን ; ” አለችው… ድሜጥሮስም “… እኔስ አንችንም ተዘምዶውንም ንቄ አይደለም … የእናት አባት ፈቃድ ልፈጽም ብዬ ነው እንጂ… ፈቃድሽማ ከኾነ በአንድ …በድንግልና አንኖርም !;… የተለያየን እንደኾን አንቺንም እኔንም ሌላ ያጋቡናል…” አላት “ ይኹን እንኑር” አለችው…
ከዚህ በኋላ በአንድ አልጋ ተኝተው… አንድ ልብስ ለብሰው… አንድ ምንጣፍ አንጥፈው አርባ ስምንት ዘመን በንጸሕና በድንግልና ኑረዋል… ይኸውም ይታወቅ ዘንድ ቅዱስ ሚካኤል መጥቶ ቀኝ ክንፉን ለእርሱ… ግራ ክንፉን ለእርሷ አልብሷቸው አድሮ… ማልዶ በመስኮት በአምሳለ ርግብ ወጥቶ ሲሔድ ያዩት ነበር…
ያን ጊዜ አባ ዮልያኖስ በእስክንድርያ የማርቆስ መንበር ዐሥራ አንደኛ ሊቀጳጳሳት ኾኖ ተሾሞ ይኖር ነበር…. አንድ ቀን ሕዝቡ ተሰብስበው “አባታችን! አንተ አረጀህ ከአንተ በኋላ የሚሾመውን ንገረን” አሉት… እርሱም “በሉ እናንተም እዘኑ” ብሏቸው ሱባዔ ገባ…
መልዐኩ ቅዱስ ሚካኤል መጥቶ… “ያለጊዜው የደረሰ ሦስት የወይን ዘለላ አስይዞ የሚመጣ አለ… ከአንተ ቀጥሎ የሚሾመው እርሱ ነው” ብሎታል… አባ ዮልያኖስም ይኽንን ለሕዝቡ ይነግራቸዋል… አይገርምም ; በነገራችን ላይ ይኽን ታሪክ እጽፍ ዘንድ ያነሣሡኝ የትርጓሜ መጽሐፍ ዕውቀታቸው የገነነላቸው ዕውቁ የአዲስ አበባው መካነ ሰማዕት ቅዱስ ቂርቆስ ደብር የመጽሐፍ ሊቅ የንታ ብርሃኑ ናቸው መምህር ብርሃኑ…..
እነሆ ታዲያ የምጽፈው ስለቅዱስ አባት ስለ አባ ድሜጥሮስ አይደለም ; ይኸ ቅዱስ ድሜጠሮስ ደግሞ ከመሾሙ አስቀድሞ ጽኮ ታጣቂ… ሞፈር አራቂ… ወይን አጽዳቂ ነበር… አንድ ቀን ወይን ለማቃናት ከተክል ቦታ ሲገባ… ያለጊዜው የደረሰ ሦስት የወይን ዘለላ አገኘ… ያን ቈርጦ አምጥቶ ለልዕልት ወይም ይሰጣታል…
እርሷም “ይህ ለእኛ አይገባም… ወስደህ ለሊቀ ጳጳሳቱ አበርክተህ… አቡነ ዘበሰማያት ተቀብለህ ና” አለችው ወስዶ ለሊቀ ጳጳሳቱ አበርክቶ.. አቡነ ዘበሰማያት ተቀብሎ ሲወጣ… አባ ዮልያኖስ ለሕዝቡ ድሜጥሮስን እያመለከተ “ከእኔ ቀጥሎ የሚሾመው ይኽ ነው” ብሏቸዋል….
አንድም… ሊቀ ጳጳሳቱ አልዋለም አላደረም ፡፡ ዕለቱን ሙቶ ቀብረውት ሲመለሱ ድሜጥሮስ ደረሰ… ሕዝቡ “ተሾምልን;” አሉት… ድሜጥሮስም የልቡን ንጽሕና በልቡ አድርጎ “ እኔ ድንቈሮው በሊቁ ወንበር ;….እኔ ባለሕጉ በንጽሑ በማርቆስ ወንበር; !… እንደምን አድርጎ ይኾናል;…አላቸው ፡፡ በነገራችን ላይ የዘንድሮ አራት ኪሎ ላይ ያለው ሹመት በአብ ዛኛው የሚገኝበት መንገድ ምን እንደኾን ታውቃላችሁ ፡፡ ስንት ልክፈልና ትሹሙኛላችሁ የሚል ነው ፡፡ ለመኾኑ የልቅናና የጵጵስና ሕልያናዊ ዋጋው ስንት ደርሶ ይኾን…..
ግን በቅዱሳኑ በእነ አባ ድሜጥሮስ ዘመን እንዲህ አልነበረም ፡፡ እግዚአብሔር ይመርጣል ፡፡ እግዚአብሔር ይሾማል ፡፡ ለዚኽ ነው ሕዝቡ ቅዱሱ አባ ድሜጥሮስን “አባታችን ዮልያኖስ ነግሮናልና… ተሾምልን…” የአሉት… እ ርሱም “እንኪያስ በሀገራችሁ ሊቀጳጳስ ሊሾም ምን ሥራ ሠርቶ ይሾማል;” አላቸው… “እንቀጸ አባግዕን አንብቦ ተርጕሞ ይስማል” አሉት…. እርሱም አንቀጸ አባግሀን አንብቦ ተርጕሞ ተሹሟል… ወዲያው ብሉይና ሐዲስ ተገ ልጾለታል…
ግን አልዘገየም ፡፡ ወዲያው ሐሜት መጣ ፡፡ ሹክሹክታ መጣ ፡፡ አዎና “የሹክሹክታ” ችግር የመጣው እንግዲህ ከዚህ በኋላ ነው… አዎ ሐሜት ተጀመረ !;… “ሹክሹክታ” ተወጠነ አይገርምም;… የአባ ድሜጥሮስን ሙያውን ንጽሕናውን ሲያዩ ጊዜ ጥቂት ሰዎች በቅንዐት ተቃጠሉ…” ሹክሹክታም “ ወደ ውስጣቸው ሠረገ አይገርምም ;… ይገርማል እንጂ….
ይልቁንም ሊቀ ጳጳሳት አባ ድሜጥሮስ ኃጢአታቸው ተገልጾለት… መንፈሳዊውን ሥርዓት ለማስከበር “አንተ በቅተሃል ተቀበል… አንተ አልበቃህም አትቀበል” እያለ ይከለክላቸው ጀመር… ይህም ንጽሕናውን … ብቃቱን የሚያሳይ ነበር ፡፡… ነገር ግን ማን ይረ ዳው;… የተገነዘበ አልነበረም… ሐሜት ብቻ ሐሜት… በእየጓዳው በእየታዛው… በእየቤቱ በእየማጀቱ ኹሉ በዝግታ ያማል… ኹሉ በቀስታ ይንሾካሾካል…. ኹሉ እየተገላመጠ ያሽሟጥ ጣል…
በቃ የሰው ነገር ይኼው ነው ፡፡ ታዲያስ…”ሹክሹክታ” ማለት ይሄ አይደል ; “ቅን ሰው ቅንነትን ይሠራ ዘንድ ይነሣል… ያንጊዜም ሹክሹክታ ይኾናል ፡፡ የማይጠቅም ሹክሹክታ ነው…” ይል ነበር ባለቅኔው ወዳጄ ገጣሚ ዮሴፍ ገዳሙ … እውነቱን እኮ ነው… ሰዎች ብዙ ጊዜ ተራራ የሚያህል የራሳቸውን ክምራዊ የኃጢአት ጕድፍ ተሸክመው… በሥውር የሐሜት “ሹክሹክታቸው” ንጹሑን ሰው ያባዝታሉ ፡፡
“ቅድመ አውፅእ ሠርዌ አምውስተ ዐይንከ—-መጀመሪያ የራስህ ጉድፍ ተመልከት ፡፡ አስወግድ”. የሚለውን ትተው…ስምህን በሐሜት ይሠልቁታል…ክብርህን “በሹክሹክታ” ይደፈጥጡታል… ምንም አይደል ወዳጄ አንባቢ ሆይ ! አንተ ብቻ ንጹሕ ኹን… ማን ያውቃል ; ንጽሕናህን ነገ ይረዱ ይኾናል…
እኔ የምለው ቅዱሱ የእስክንድርያው ሊቀጳጳሳት አባ ድሜጥሮስ በጊዜው ስለቀረበበት “ሹክሹክታ” ምን መለሰ”… ይህ ቅዱስ አባት ንጽሕናውን ገለጸላቸው ;… ወይስ ዝም አለ ; የዚህ ኹሉ …”ሹክሹክታ” መጨረሻው ምን ይኾን ;… መልሱን ለማግኘት የዚህን ታሪክ የመጨረሻውን መጨረሻ ክፍል በሚቀጥለው ብንቀጥልስ ;…አይሻልምን ፡፡ ይሻላል ፡፡ ቸር ሰንብቱ…ቸር ጊዜ…ቸር ዘመን ለኹላችን………….
ይቀጥላል……

ተጻፈ
በወርኃ ጳጕሜን 6 2011 ዓመተ ምሕረት
አዲስ አበባ—–ኢትዮጵያ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *