ማዕተበ ጸሎት

ከሊቀ ሊቃውንት አለቃ አያሌው ታምሩ

                          ሰማዕት ዘእንበለ ደም                        

            አቤቱ አምላኬና ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ !! የእናትህ ድንግል ማርያም ርስትና የአንተም ርስት ስለኾነች እጆቿን ወደአንተ ስለምትዘረጋ ቅድስት ሀገርህ ኢትዮጵያና በባሕርይ አባቱ እግዚአብሔር ዕሪና የነበረና የአለ የሚኖር ወልድ ዋህድ ብላ ስለምታምን ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንህ ወደ አንተ የምጮኸው ፍጹም ልመናዬን ስማኝ ፡፡

            እነሆ አፅራረ ክርስቲያን የኾኑ ጠላቶችህ ኑ የክርስቲያን ስማቸው ከእግዚ አብሔር ሕዝብነት እንዳይቈጠር ከሕዝብ እንለያቸው ብለው በንዑዳን ክቡራን ወገኖችህ ኢትዮጵያ ውያን ላይ ክፉ ምክርን መክረዋልና ፡፡ በመገዳደርና በማስፈራራትም ደንፍተዋልና አቤቱ ስለቅድስት ሀገር ኢትዮጵያና ስለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስለመምህራኗና ስለምእመናኗ ክብርና ልዕልና የልቡናዬን መሻት ፈጽምልኝ ፡፡ ልመናዬንም ፈጽመህ ስማኝ ፡፡

            አቤቱ በክቡር ደምህ ፈሳሽነት ቤዛ ትኾናት ዘንድ ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ብለህ በጲላጦስ ዐደባባይ የተገረፍህ እንደአንተ የአለ ማንም የለምና ጩኸቴን ችላ አትበል ፡፡ አቤቱ ምንም ምን በደል ሳይኖርብህ ስለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ብለህ መከራ መስቀልን የተቀበልህ የርኵሳን አይሁድ ምራቅን የታገሥህ አምላኬ ሆይ እንደ አንተ የአለ ማንም የለምና ጩኸቴን አድምጥ ፡፡  

           አቤቱ ስለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ብለህ በዕፀ መስቀል ላይ ተሰቅለህ ኀፍረተ መስቀልን የታገሥህ እንደ አንተ የአለ ማንም የለምና ልመናዬን ችላ አትበል ፡፡

           እነሆ አፅራረ ቤተ ክርስቲያን በአንድነት ተሰብስበው መክረውብናልና በአንተም ላይ አንድ ኾነው በዓመፃ ተነሥተዋልና ልመናዬን ችላ አትበል ፡፡ አቤቱ ኃይልህንና ገናንነትህ ገልጸህ የወደቀችውን ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያን አንሣ ፡፡ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሕጓ ሥርዓቷ ተመልሶ ይጸና ዘንድ ርዳን ፡፡

           አቤቱ ወልድ ዋህድ አምላከ ኢትዮጵያ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ !! አንተ ኹሉን ማድረግ የሚቻልህ ምንም ምን የሚሳንህ የሌለ ፍጹም የባሕርይ አምላክ እንደ ኾንህ ፍጥረት ኹሉ ያውቁ ዘንድ ስለ እናትህ ቅድስት ድንግል ማርያምና ስለወዳጅህ ቅዱስ ዳዊት ብለህም ይኽቺ ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያን በይቅርታህ ጐብኛት ፡፡ ርዳት ፡፡ ከክፉም ኹሉ ጠብቃት ፡፡

          አቤቱ ስለ ኦርቶዳክሳዊት ተዋህዶ ሃይማኖትና ስለ ቅድስት ሀገሬ ኢትዮጵያ ብዬ በጥልቅ ጽንዐ መከራ ውስጥ ጠርቼሃለሁና ቃሌን ስማኝ ፡፡ ፈቃደ ርኅራኄህም የልመናዬን ቃል ያድምጥ ፡፡ አቤቱ የበደለኛን በደል ብታስብስ በፊትህ ፍጥረት ኹሉ መቆም ባልተቻለውም ነበር ፡፡ ነገር ግን ከአንተ ዘንድ የሚገኝ ይቅርታህ እጅግ የበዛ ነውና ስለቅዱስ ስምህ ብለህ የልቡናየን መሻት እንድትፈጽምልኝ እታመንብሃለሁ ፡፡

          ንጉሤና አምላኬ ወልድ ዋህድ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ !! ለዘለዓለም ከፍ ከፍ አድርግሃለሁ ፡፡ ቅዱስ ስምህንም አመሰግናለሁ ፡፡ ስብሐት ለአብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ ለዓለም ወለዓለመ ዓለም አሜን ፡፡                                               

          ይኽንን «ማዕተበ ጸሎት» የተሰኘ የክርስትና ጸሎት ስለቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ሃይማኖታችንና ስለቅድስት ሀገራችን ኢትዮጵያ ወደፈጣሪያቸው የጸለዩትና በመልዕክተ መንፈስቅዱስ መጽሐፋቸው ገጽ ፪፻፳፩ (221) በልሳነ ግእዝ የአቀረቡት ኢትዮጵያዊው ሊቅ ሰማዕት ዘእንበለ ደም ሊቀ ሊቃውንት አያሌው ታምሩ በዚኹ የመጽሐፋቸው መደምደሚያ ላይም ለእኛ ኢትዮጵያውያን ልጆቻቸው የሚመለከተውን አባታዊ መልዕክት አስተላልፈው ነበር ፡፡

 መልዕክታቸውም

           “…ኢትዮጵያውያን ኹሉ ወደታላቂቱ ሀገራችሁ ወደተቀደሰችው ቤተ ክርስቲያናችሁ ወደ እውነተኛይቱ ሃይማኖታችሁ እንድትመለሱና እንድትድኑ እኔ አነስተኛው ደካማ ወንድማችሁ በጌታ ችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተማፅኜ እለምናችኋለሁ ፡፡ እርሱም መንገዱን ይምራችሁ ፡፡ ብርሃኑን ያብራ ላችሁ ፡፡ ቸር ነውና ፡፡ ምሕረቱም ለዘለዓለም ነውና ፡፡ ምስጋና ለእርሱ ይኹን አሜን ፡፡…”

 

ምንጭ = ከመልዕክተ መንፈስ ቅዱስ መጽሓፋቸው                                   

                                  ተርጓሚ

                                  የቅኔው ንጉሥ የትርጓሜው ጌታ

                                    ፪፼፲ወ፪ ዓመተ ምሕረት

                                        ዘዋድላ ወዘዋሸራ

                                           ኢትዮጵያ

                                           

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *